ፅዱ እና ጤናማ አካባቢን ለትውልድ ለማስተላለፍ በሚደረገው ጥረት የሁሉም ተሳትፎ እና እገዛ ሊኖር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ፅዱ እና ጤናማ አካባቢን ለትውልድ ለማስተላለፍ በሚደረገው ጥረት የሁሉም ተሳትፎ እና እገዛ ሊኖር ይገባል

ሀረር ፤ ሰኔ 22/2017(ኢዜአ)፦ፅዱ እና ጤናማ አካባቢን ለትውልድ ለማስተላለፍ በሚደረገው ጥረት የሁሉም ተሳትፎ እና እገዛ ሊኖር ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ለሊሴ ነሜ ተናገሩ።
ሁለተኛው ዙር የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ በሐረሪ ክልል በይፋ ተጀምሯል።
በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ለሊሴ ነሜ፤ የኢትዮጵያን ጽዳትና ውበት በጋራ በመጠበቅና በመንከባከብ ምቹና ተመራጭ ማድረግ የዜጎች ሁሉ ሃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጀመረው "ፅዱ ኢትዮጵያ" ንቅናቄ አላማው ይሄው መሆኑን አንስተው ለስኬቱ መረባረብ ይጠበቅብናል ብለዋል።
በሁሉም የሀገሪቷ አካባቢዎች ፅዱ እና ለመኖር ምቹ የሆኑ ከተሞችን በመፍጠርና የአረንጓዴ አሻራ ስራዎችን በማጠናከር ብዙ መስራት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
በኮሪደር ልማትና ኢኮ ቱሪዝም ዘርፍ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማስፋት፣ የወንዞች ዳርቻን በማጽዳትና መልሶ በማልማት ምቹና ውብ መኖሪያ የማድረግ ጉዳይ ለነገ የሚተው ስራ አይደለም ብለዋል።
በዚህ ረገድ በመጀመሪያው ዙር የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን አስታውሰው በሁለተኛውም የተሻለ ስኬት ለማስመዝገብ ተዘጋጅተናል ሲሉ አረጋግጠዋል።
በመሆኑም ለስድስት ወራት በሚከናወነው ሁለተኛው ዙር የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የሐረሪ ክልል አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ነቢላ መሃዲ ሐረርን ውብ እና ፅዱ የማድረግ ጥረታችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጌቱ ወየሳ በበኩላቸው ሐረርን ውብ እና ፅዱ በማድረግ ሂደት ህብረተሰቡ ተሳትፎውን ሊያጠናክር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በመድረኩ የባለስልጣኑ አመራርና ሰራተኞች፣ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና ሌሎችም እንግዶች የተገኙ ሲሆን በእለቱ የችግኝ ተከላ አካሂደዋል።