በመዲናዋ ሁለተኛው ዙር የፅዱ ኢትዮጵያ ከተማ አቀፍ ንቅናቄ በይፋ ተጀመረ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 21/2017(ኢዜአ)፦ በመዲናዋ የ90 ቀን ልዩ የንቅናቄ አጀንዳ አካል የሆነው የፅዱ ኢትዮጵያ ከተማ አቀፍ ንቅናቄ "ፅዱ፥ ውብ እና ደህንነቷ የተጠበቀች አዲስ አበባ" በሚል መሪ ሀሳብ በይፋ ተጀምሯል።

በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ የፌዴራልና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች፣ የሲቪክ ማህበራት ተወካዮች፣ ተፅእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፤ የዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎችና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

የፌዴራል የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ የሁሉም ዜጋ ሃላፊነት ነው ብለዋል።


 

የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ከብክለት የጸዳ አካባቢያዊ ሥርዓተ ምህዳር እየፈጠረ መምጣቱንም ገልጸዋል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ በበኩላቸው፥ ንቅናቄው መዲናዋን ፅዱና ከብክለት የፀዳች በማድረግ በኩል ትልቅ ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል።

ህዝቡም በአካባቢ ጥበቃ እንቅስቃሴ ላይ በንቃት እንዲሳተፍ ዕድል መፍጠሩን ጠቁመዋል።


 

በአካባቢ ጥበቃና በብክለት ዙሪያ ለማህበረሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ በንቅናቄው ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ተጠቃሽ መሆኑን ተናግረዋል።

በንቅናቄው የአፈር፣ የውሀ፣ የፕላስቲክ፣ የአካባቢ ብክለትን ለማስቀረት የጽዳት ዘመቻ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫና ሌሎች ተግባራት እንደሚከናወኑ ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም