የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የማንሰራራት ጉዞ እንዲሳካ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው- ሚኒስትሮች

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 23/2017(ኢዜአ)፦ የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር  የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የማንሰራራት ጉዞ እንዲሳካ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ  መሆኑን ሚኒስትሮች ገለጹ።  

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት ካሺም ሼቲማ፣ የፌደራልና የክልል መንግሥታት ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በአዲስ አበባ የወንዝ ዳር ዳርቻ ልማት የችግኝ የተከላ መርሐ ግብር መካሄዱ ይታወቃል።    

በመርሐ ግብሩ ላይ የተሳተፉ ሚኒስትሮች እንደገለጹት፥ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ኢኮኖሚው እንዲያንሰራራ የተያዙ ግቦችን ለማሳካት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።  

አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለቀጣዩ ትውልድ የተበረከተ ስጦታ መሆኑን ጠቁመው መርሐ ግብሩ ተጨባጭ ውጤቶች እየተገኙበት መሆኑንም አንስተዋል።  

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ደ/ር) እንዳሉት፤ ባለፉት 6 ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል።    


 

ኢኮኖሚው ፈጣንና ተከታታይ እድገት እያስመዘገበ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፥  የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።  

በመርሐ ግብሩ በርካታ የቡና ችግኞች መተከላቸውን ገልጸው ይህም ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ ከቡና የምታገኘው የውጭ ንግድ ገቢ እየጨመረ እንዲመጣ ማስቻሉን ተናግረዋል።     

አቮካዶን ጨምሮ የተለያዩ የፍራፍሬ ምርቶች ወደ ውጭ በመላክ ገቢ እየተገኘ  መሆኑን ጠቅሰው፥ የሌማት ትሩፋት ግቡን እንዲመታ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ጉልህ ሚና አለው ብለዋል።

አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ በሚደረገው ሀገራዊ ጥረት ውስጥ የማይተካ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።

የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ በበኩላቸው አረንጓዴ አሻራ ለትውልድ የሚበረከት ስጦታ ነው ብለዋል። 

የአረንጓዴ አሻራ ትሩፋት እየታየ መሆኑን ጠቅሰው፥ ኢኮኖሚው እንዲሳለጥ ከማገዝ ባለፈ ለኑሮ ምቹ ከባቢን እየፈጠረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።


 

የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)፤ አረንጓዴ አሻራ የከርሰ ምድር እና ገጸ-ምድር ውሃ እንዲጨምር እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።


 

መርሐ ግብሩ ምንጮች እንዲጎለበቱ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው ደርቆ የነበረው የሀረማያ ሀይቅ ማገገምና ማንሰራራት የአረንጓዴ አሻራ ውጤት መሆኑን አስረድተዋል።  

አፈር እንዳይሸረሸርና ግድቦች በደለል እንዳይሞሉም መርሃ ግብሩ ትልቅ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች እንደሚተከሉም ተገልጿል።

          

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም