አረንጓዴ አሻራን በማኖር የተሻለች ሀገር ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ለሚደረገው ጥረት ስኬት ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል - የኃይማኖት አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
አረንጓዴ አሻራን በማኖር የተሻለች ሀገር ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ለሚደረገው ጥረት ስኬት ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል - የኃይማኖት አባቶች

አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 22/2017(ኢዜአ)፦አረንጓዴ አሻራን በማኖር የተሻለች ሀገር ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ለሚደረገው ጥረት ስኬት ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ የኃይማኖት አባቶች ተናገሩ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ የ7ኛው የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሐግብር "በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሃሳብ ተካሂዷል።
መርሀግብሩን ተከትሎም ከከተማዋ የተወጣጡ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል፡፡
የተለያዩ የኃይማኖት አባቶችም አረንጓዴ አሻራቸውን ያኖሩ ሲሆኑ ትውልዱ ችግኝ በመትከል የተሻለች ሀገር ለማስተላለፍ መትጋት እንዳለበት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርሰቲያን የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ በርተሎሜዎስ፤ እንደ ሀገር አረንጓዴ አሻራ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
አረንጓዴ አሻራ የሀገርን ገጽታ በእጅጉ እየቀየረ የሚገኙ መሆኑን አንስተው፤ ጽዱና ለነዋሪዎች ምቹ የሆነች ሀገር ከመገንባት አንጻርም ትልቅ ተስፋ መታየቱን ገልጸዋል፡፡
የሁሉም ቤተ እምነት ተከታዮችም የአረንጓዴ አሻራ ስራን በማከናወን ለመጪው ትውልድ የተሻለች ሀገር ለማስተላለፍ የሚደረገውን ጥረት ማገዝ እንዳለባቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሱልጣን አማን ኤባ እንዳሉትም፤ የአረንጓዴ አሻራ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያየ እውቅና እንድታገኝ ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡
መጪው ትውልድ የተራቆተች ሀገር እንዳይረከብ እና አሁን ያለው ትውልድም ጤናው ተጠብቆ ምቹ አካባቢ እንዲኖር ለማስቻል የአረንጓዴ አሻራ ስራዎች መጠናከር እንደሚገባቸውም ገልጸዋል፡፡
የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ ለፍሬ ማብቃት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ሉተራን ቤተክርስቲያን መሪ ቄስ ሙሴ አላዓዛር እንዳሉትም፤ የአረንጓዴ አሻራ አካባቢን ጽዱና ውብ በማድረግ ገጽታን የሚለውጥ በመሆኑ ሁሉም ሰው በዚህ ተግባር መሳተፍ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ በበኩላቸው፤ በዛሬው ዕለት ከሁሉም ቤተ እምነቶች የተወጣጡ አባቶች የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ላይ መሳተፋቸውን ተናግረዋል፡፡
ትውልዱም የኃይማኖት አባቶቹን አርዓያ በመከተል የአረንጓዴ አሻራውን ማሳረፍ እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡