በአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ለተያዘው ዕቅድ ስኬታማነት ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል

አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 22/2017(ኢዜአ)፦በአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ ለተያዘው ዕቅድ ስኬታማነት ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ፡፡ 

በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ የ7ኛው የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሀግብር "በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሃሳብ ተካሂዷል።

መርሀግብሩን ተከትሎም ከከተማዋ የተወጣጡ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል፡፡


 

በዚሁ ወቅት ኢዜአ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ያለ አንዳች ልዩነት መከናወን የሚገባው የሁሉም ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡ 

የወሎ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ነጻነት ጣሰው እንዳሉትም፤ ለ7ኛ ጊዜ እየተከናወነ በሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ሁሉም ያለ አንዳች  ልዩነት መሳተፍ ይገባዋል ብለዋል፡፡

የአሁኑ ትውልድ ችግኝ ሲተክል ከራሱ አልፎ ለመጪው ትውልድ የማሰቡ ማሳያ ነው ያሉት አቶ ነጻነት ችግኝ በመትከል ሀገርን አረንጓዴ የማልበስ ግቡ እንዲሳካ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

ችግኝ በመትከል ለመጪው ትውልድ የለመለመችና ምቹ አየር ያላት ሀገርን ለማስረከብ ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ዋና ጸሐፊ አቶ ክፍለማርያም ሙሉጌታ በበኩላቸው፤ የአረንጓዴ አሻራ የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ረገድ የማይተካ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ብለዋል፡፡


 

ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን ተንከባክቦ ማጽደቅ የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ኃላፊነት መሆን እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡

በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ለተያዘው ዕቅድ ስኬታማነት ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም