የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከአካባቢ ጥበቃ ባሻገር የዜጎችን ተጠቃሚነት እያሻሻለ ይገኛል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከአካባቢ ጥበቃ ባሻገር የዜጎችን ተጠቃሚነት እያሻሻለ ይገኛል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 21/2017(ኢዜአ)፦የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከአካባቢ ጥበቃ ባሻገር የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያሻሻለ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት ካሺም ሼቲማን እንዲሁም ሌሎች የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላትና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ትናንት ተካሂዷል።
በዛሬው ዕለትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት ካሺም ሼቲማን፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳደሮች፣ የሁለቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች እንዲሁም ሚኒስትሮች በተገኙበት በአዲስ አበባ የወንዝ ዳር ዳርቻ ልማት የችግኝ የተከላ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማንሰራራት የሚያሳልጥ ሀገራዊ ፕሮጀክት ነው።
መርሃ ግብሩ በተለይ የአዲስ አበባን የአረንጓዴ ሽፋን በማሳደግ ገጽታዋን በመቀየር ረገድ ትልቅ ፋይዳ ማበርከቱንም ነው የገለጹት።
የአዲስ አበባ ከተማ የደን ሽፋን ከዚህ ቀደም ከነበረበት ሁለት ነጥብ ስምንት በመቶ ወደ 22 በመቶ ማደጉን አንስተው፤ ይህም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተጨባጭ ውጤትን እንደሚያሳይ ተናግረዋል።
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ችግኝ ከማዘጋጀት እስከ መንከባከብ ባለው ሰንሰለት ውስጥ ለበርካታ ወጣቶች የስራ ዕድል መፈጠሩንም ጠቁመዋል።
በአዲስ አበባ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ከወንዝ ዳር ልማት ጋር በማስተሳሰር እየተተገበረ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም በተለይ ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞች በስፋት እየተተከሉ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በጎ ሚና እንዳለው አንስተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ በከተማ ደረጃ በነገው ዕለት የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብርን እንደሚያስጀምር ያነሱት ከንቲባ አዳነች፤ የከተማዋ ነዋሪዎች በመርሃ ግብሩ በንቃት እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተግቶ በመስራት ሀገርን መለወጥና ለመጪው ትውልድ ዕዳን ሳይሆን ምንዳን ማውረስ እንደሚገባ በተግባር የሚታይበት እንደሆነም ነው የገለጹት።
"በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሃሳብ በሚካሄደው በዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች ይተከላሉ።