በደቡብ ወሎ ዞን ከ29 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል

ደሴ ፤ ሰኔ 21/2017(ኢዜአ)፡-በደቡብ ወሎ ዞን  በአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር  ከ29 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ  ችግኝ ለመትከል ዝግጅት መደረጉን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

ከዝግጅቱም መካከል  የችግኝና የመትከያ ጉድጓድ ቁፋሮ ማካሄድ እንደሚገኙበት መምሪያው ጠቅሷል። 

የመምሪያው ምክትል ኃላፊ አቶ ደመቀ አድማሱ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር  በዞኑ ጉዳት ደርሶበት የቆየ  ደን እንዲያገግም ፣ መሬቱ በጎርፍ እንዳይሸረሸርና ምርታማነት እንዲጨምር እያስቻለ ነው።


 

ሕብረተሰቡም ከደን ልማቱ የሚያገኘውን ጥቅም ለማስፋት ችግኝ የመትከልና የመንከባከብ ባሕሉ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል። 

በክረምቱ በሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር  በርካታ ችግኝና ጉድጓድ   ተቆፍሮ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡

ችግኙ  በ29 ሺህ 673 ሄክታር መሬት ላይ እንደሚተከል ጠቁመው፤ ሕብረተሰቡም ከመትከል ባለፈ በኃላፊነት በመንከባከብ ተጠቃሚነቱን በተግባር እያረጋገጠ ነው ብለዋል፡፡

በቃሉ ወረዳ የ06 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ይማም ካሳው በሰጡት አስተያየት፤ ከአሁን ቀደም የተለያዩ የፍራፍሬ ችግኝ በማፍላት በማሳቸው ላይ ከመትከል ባለፈ ችግኝ እየሸጡ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡


 

ዘንድሮም ከ20 ሺህ በላይ የማንጎ፣ አቡካዶና ሌላም  የፍራፍሬ ችግኝ ያዘጋጁ መሆኑን ጠቁመዋል። 

ተሁለደሬ ወረዳ የ09 ቀበሌ  አርሶ አደር ያሲን ጅብሪል በበኩላቸው ፤ በዘንድሮው ክረምት የሚተከል የባህርዛፍ፣ ጽድና ሌላም ዓይነት ችግኝ ለተከላ ች እያዘጋጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከሚተክሉት የተረፈውን በመሸጠም ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ማቀዳቻውንም ጠቁመዋል፡፡

በደቡብ ወሎ ዞን ባለፈው ክረምት 30 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ላይ ከተተከለው ችግኝ ውስጥ 80 በመቶው መፅደቅ መቻሉን ከግብርና መምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም