የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአካባቢ መራቆትን ከመከላከል ባሻገር በፍራፍሬ ልማት ላይ ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል- የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች

አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 22/2017(ኢዜአ)፦የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአካባቢ መራቆትን ከመከላከል ባሻገር በፍራፍሬ ልማት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ገለጹ።

ክልሎች ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ስኬታማነት የተሻለ ዝግጅት ማድረጋቸውንም ነው ርዕሳነ መስተዳደሮቹ ያረጋገጡት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት ካሺም ሼቲማን ፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የሁለቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች እንዲሁም ሚኒስትሮች በተገኙበት በአዲስ አበባ የወንዝ ዳር ዳርቻ ልማት  የችግኝ የተከላ መርሃ ግብር ተካሄዷል።

በመርሃ ግብሩ የተገኙ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች እንዳሉት፤ የአረንጓዴ አሻራ ዜጎች በተደመረ አቅም ኢትዮጵያን ለመለወጥ በጋራ የቆሙበት ሀገራዊ የልማት አጀንዳ መሆኑን አብራርተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ፤ በክልሉ በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በመርሃ ግብሩ የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብረ አማካኝነትም በክልሉ ተራቁተው የነበሩ አካባቢዎች መልሰው ማገገማቸውን ጠቅሰው፤ ከሀገር ውስጥ ባለፈ  ለውጭ ገበያ የሚቀርብ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርታማነት አቅም መፈጠሩንም ገልጸዋል።

በዘንድሮው ዓመትም የክልሉ ነዋሪዎች በመርሃ ግብሩ ላይ በስፋት እንዲሳተፉ የሚያደርግ ዝግጅት መጠናቀቁን በመጠቆም።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ በበኩላቸው፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በርካታ ህዝብ በማሳተፍ ለውጥ ማምጣት መቻሉን ተናግረዋል።


 

መርሃ ግብሩ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው ጠቅሰው፤ በትግራይ ክልል ሐምሌ 20 ቀን 2017 ዓ.ም መርሃ ግብሩ በይፋ እንደሚጀመር ጠቁመዋል።ለዚሁ ስራ የሚውል የችግኝ ዝግጅት መደረጉንም ነው የገለጹት። 

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተለያዩ የፍራፍሬ አይነቶችን በሀገር አቀፍ ደረጃ ማስፋት ያስቻለ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሌ ሀሰን ናቸው።


 

መርሃ ግብሩ ከቡና በተጨማሪ ኢትዮጵያ በፍራፍሬ ኤክስፖርት እንድትታወቅ እያደረጋት ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

የአረንጓዴ አሻራ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለሚገኝበት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ትልቅ ትርጉም እንዳለው ጠቅሰው፤ የክልሉ ነዋሪዎች በመርሃ ግብሩ የሚያደርጉት ተሳትፎ መጨመሩንም ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም