ችግኝ በመትከል ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ የመገንባት ተግባራችንን እናጠናክራለን - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ችግኝ በመትከል ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ የመገንባት ተግባራችንን እናጠናክራለን - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 22/2017(ኢዜአ)፦ችግኝ በመትከል ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ የመገንባት ተግባራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ የ7ኛው የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሀግብር "በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሃሳብ ተካሄዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት፤ ባለፋት ስድስት ዓመታት ሁሉም ኢትዮጵያውያን ተሳትፈው 40 ቢሊዮን ችግኞችን መትከላቸውን ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃም ባለፉት ስድስት ዓመታት 85 ሚሊዮን ችግኞች መተከላቸውን ጠቁመው፤ የከተማዋ የደን ሽፋንም ከ2 ነጥብ 8 በመቶ አሁን ላይ 22 በመቶ መድረስ መቻሉን ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ ስራዎች ወንዞች ማንሰራራት ጀምረዋል፣ በአፈርና ውሃ ጥበቃ ውጤቶችም መታየት መጀመራቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ችግኝ በመትከል ተረጂነትን ታሪክ ለማድረግ እየሰራች ነው ያሉት ከንቲባዋ፤ በአዲስ አበባ ለዘንድሮው ተከላ 916 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።
ችግኝ በመትከል ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ የመገንባት ተግባራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ አረጋግጠዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ግርማ ሰይፉ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አሁን ያለው ትውልድ ለመጪው የምትሆን ሀገርን የመፍጠር ማሣያ ነው ብለዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የኢትዮጵያን የከፍታ ጉዞ የሚያስቀምጥ ለተጀመረው የሀገር ግንባታ ሂደት ቀጣይነት መሠረት የሚጥል መሆኑንም ተናግረዋል።
አረንጓዴ አሻራ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ያነሱት የቢሮ ሃላፊው በከተማ ደረጃ ይህንን ለማረጋገጥ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በከተማ ደረጃ የተያዘውን ግብ በማሳካት አረንጓዴ አሻራ ለአካባቢ ውበትና ለጤና መሠረት መሆኑን በተግባር እናረጋግጣለን ብለዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ማስጀመሪያ መርሃግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት መካሄዱ ይታወቃል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ "በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሃሳብ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች እንደሚተከሉም ይታወቃል።