አዲስ አበባን ምቹ እና ጽዱ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባን ምቹ እና ጽዱ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 22/2017 (ኢዜአ) አዲስ አበባን ለመኖር ምቹ እና ጽዱ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ የ7ኛው የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሐግብር "በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ይገኛል።
በመርሐግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ቡዜና አልከድር፣ በብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሞገስ ባልቻ፣ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ የስፖርት ማህበረሰብ ፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች፣ የጤናና የትምህርት ማህበረሰብ፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮችን ጨምሮ ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ አካላት ተገኝተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት፤ ባለፋት ስድስት ዓመታት ሁሉም ኢትዮጵያውያን ተሳትፈው 40 ቢሊዮን ችግኞችን መትከላቸውን ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃም ባለፉት ስድስት ዓመታት 85 ሚሊዮን ችግኞች መተከላቸውን ጠቁመው፤ የከተማዋ የደን ሽፋንም ከ2 ነጥብ 8 በመቶ አሁን ላይ 22 በመቶ መድረስ መቻሉን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ችግኞችን በመትከል ተረጂነትን ታሪክ ለማድረግ እየሰራች ነው ያሉት ከንቲባዋ፤ በአዲስ አበባ ለዘንድሮው ተከላ 916 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።
በመትከል ለአየር ንበረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ እንደሚገነባ የጠቆሙት ከንቲባዋ፤ አዲስ አበባን ለመኖር ምቹ እና ጽዱ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ ስራዎች ወንዞች ማንሰራራት ጀምረዋል፣ በአፈርና ውሃ ጥበቃም ውጤቶችም መታየት መጀመራቸውን ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ግርማ ሰይፉ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አሁን ያለው ትውልድ ለመጪው የምትሆን ሀገርን የመፍጠር ማሣያ ነው ብለዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የኢትዮጵያን የከፍታ ጉዞ የሚያስቀምጥ ለተጀመረው የሀገር ግንባታ ሂደት ቀጣይነት መሠረት የሚጥል መሆኑንም ተናግረዋል።
አረንጓዴ አሻራ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ያነሱት የቢሮ ኃላፊው በከተማ ደረጃ ይህንን ለማረጋገጥ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በከተማ ደረጃ የተያዘውን ግብ በማሳካት አረንጓዴ አሻራ ለአካባቢ ውበትና ለጤና መሠረት መሆኑን በተግባር እናረጋግጣለን ብለዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ማስጀመሪያ መርሐግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት መካሄዱ ይታወቃል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ "በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሃሳብ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች እንደሚተከሉም ይታወቃል።