የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሁሉም ዜጋ ሀገር ለመለወጥ በባለቤትነት የሚሳተፍበት የትውልድ አሻራ ነው - አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 21/2017(ኢዜአ)፦ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሁሉም ዜጋ ሀገር ለመለወጥ በባለቤትነት የሚሳተፍበት የትውልድ አሻራ መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት ካሺም ሼቲማን እንዲሁም ሌሎች የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላትና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ትናንት ተካሂዷል። 


 

በዛሬው ዕለትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት ካሺም ሼቲማን፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳደሮች፣ የሁለቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች እንዲሁም ሚኒስትሮች በተገኙበት በአዲስ አበባ የወንዝ ዳር ዳርቻ ልማት  የችግኝ የተከላ መርሃ ግብር ተካሂዷል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በመርሃ ግብሩ ላይ እንደገለጹት፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ ልማት ጋር የተሳሰረ ነው።

የአየር ንብረት ለውጥ በምርታማነት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እንዳለው ጠቁመው፤ ከዚህ አኳያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አካባቢን ከመለወጥ ባሻገር ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማንሰራራት ትልቅ ሚና እንዳለው አብራርተዋል።

ከአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተጀመረ ወዲህ ኢትዮጵያ በቡና ምርታማነት ላይ ያስመዘገበችው ውጤት ለዚህ ማሳያ መሆኑን በማንሳት።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሁሉም ዜጋ ሀገር ለመለወጥ በባለቤትነት የሚሳተፍበት የትውልድ ስራ መሆኑንም ተናግረዋል።


 

በዚህ ረገድ ሁሉም የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ አፈ ጉባኤ ታገሰ ጥሪ አቅርበዋል።

ሁሉም ዜጋ እጅ ለእጅ ተያይዞ በጋራ መስራት ከቻለ ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ  እንደምትለወጥ ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ የተጀመሩ ስራዎችን በትብብር ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

"በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሃሳብ በሚካሄደው በዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች  ይተከላሉ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም