በሲዳማ ክልል የአረንጓዴ አሻራ ልማት ውጤቶችን በማስቀጠል የመሬት መንሸራተትና የጎርፍ አደጋን ለመከላከል እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል የአረንጓዴ አሻራ ልማት ውጤቶችን በማስቀጠል የመሬት መንሸራተትና የጎርፍ አደጋን ለመከላከል እየተሰራ ነው

ሀዋሳ፤ ሰኔ 23/2017 (ኢዜአ)፡-በሲዳማ ክልል በአረንጓዴ አሻራ ልማት የተገኙ ውጤቶችን በማስቀጠል የመሬት መንሸራተትና የጎርፍ አደጋን በዘላቂነት ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።
''በመትከል ማንሰራራት'' በሚል መሪ ቃል ክልላዊ የአረንጓዴ አሻራ ልማት በዳራ ኦቲልቾ ወረዳ ሾይቾ ቀበሌ ዛሬ ተጀምሯል፡፡
ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በእዚህ ወቅት እንደገለጹት በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ሥራዎች ዘርፈ ብዙ ውጤቶች ተመዝግዋል፡፡
በዚህም የተራቆቱ መሬቶች፣ የደረቁ ወንዞችና ጅረቶች መልሰው በማገገማቸው የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባሻገር ምርታማነት ለመጨመርና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እያስቻሉ መሆኑን ገልጸዋል።
በአረንጓዴ አሻራ ልማት የተገኙ ውጤቶችን ቀጣይነት በማረጋገጥ በክልሉ ሊገጥም የሚችለውን የመሬት መንሸራተትና የጎርፍ አደጋ ለመከላከል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ ልማት የክልሉ ህዝብና መንግስት የህልውና ጉዳይ ነው ያሉት አቶ ደስታ፣ ልማቱ ባህል እየሆነ በመምጣቱ ለትውልድ እንዲሻገር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ልማት ሥራ የህዝቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም አቶ ደስታ ገልጸዋል፡፡
ዛሬ ክልላዊ የአረንጓዴ አሻራ ልማት የተጀመረበት ቀበሌ ከዚህ ቀደም የተራቆተ እንደነበር አስታውሰው፣ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የልማት ሥራዎች የአካባቢው ስነምህዳር መቀየሩንም ጠቅሰዋል፡፡
የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ሃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ በበኩላቸው በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ልማት ከ23 ሺህ 200 ሄክታር በላይ መሬት በአረንጓዴ ለማልማት ታቅዶ ወደስራ ተገብቷል፡፡
በክልሉ በመርሃ ግብሩ ከሚተከሉ ችግኞች 60 ከመቶ የሚሆኑት ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚሰጡና ቡና ቀዳሚው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የደን ሽፋንን የሚያሳድጉ፣ ለምግብነትና ለእንሳሰት መኖነት የሚውሉ እንዲሁም ለኢኮ ቱሪዝም የሚጠቅሙ ችግኞች መዘጋጀታቸውን ጠቅሰው፣ ለሚተከሉ ችግኞች ህዝቡን ባለቤት ለማድረግ ይሰራል ብለዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት የተተከሉ ችግኞች የደን ሽፋንን በማሳደግ፣ የተጎዱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ በማድረግና እና የመሬት ለምነትን በመጨመር ምርታማነትን አሳድገዋል ሲሉም ሃላፊው ተናግረዋል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ ልማት ትውልድንና ሃገርና የሚያስቀጥል ሥራ በመሆኑ ሁሉም በሃላፊነት እየተሳተፈ መሆኑንና እሳቸውም የድርሻቸውን ለመወጣት በመርሃ ግብሩ መገኘታቸውን የተናገሩት ደግሞ በኩረ ትጉሃን ቀሲስ አማረ ግርማ ናቸው፡፡
ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን በማኖራቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው፣ የተተከሉ ችግኞችን በአግባቡ መንከባከብ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ የክልሉ ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ መንግስት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡