ችግኝ በመትከል ጤንነቱ የተጠበቀ ትውልድ ለመፍጠር ሁሉም ሊረባረብ ይገባል - የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች - ኢዜአ አማርኛ
ችግኝ በመትከል ጤንነቱ የተጠበቀ ትውልድ ለመፍጠር ሁሉም ሊረባረብ ይገባል - የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች

አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 22/2017(ኢዜአ)፦በአረንጓዴ አሻራ ውብና ንጹህ ከባቢን በመፍጠር ጤንነቱ የተጠበቀ ትውልድ እንዲኖር ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ የ7ኛው የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር "በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሃሳብ ተካሂዷል።
መርሐ ግብሩን ተከትሎም ከከተማዋ የተወጣጡ በርካታ የማህበረሰብ ክፍሎች አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል፡፡
በዚሁ ወቅት ኢዜአ ያነጋገራቸው አትሌቶች፣ አርቲስቶች እና የጤና ባለሙያዎች የአረንጓዴ አሻራ የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ረገድ ጉልህ ሚና አለው ብለዋል፡፡
ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ በሁሉም ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ላይ መሳተፍ በመቻሏ የተሰማትን ደስታ ገልጻለች፡፡
አረንጓዴ አሻራ ዘርፍ ብዙ ጠቀሜታን የሚያስገኝ ነው ያለችው ኮማንደር ደራርቱ፤ በተለይም አትሌቶች በልምምድ ቦታ ጥሩ አየር ተንፍሰው ለድል እንዲበቁ ከማድረግ አኳያ ሚናው ከፍተኛ ነው ብላለች፡፡
በስፖርቱ ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎች የአረንጓዴ አሻራን በማኖር ሀገር የያዘችው ግብ ስኬታማ እንዲሆን የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ብላለች፡፡
አርቲስት የትናየት ታምራት በበኩሏ፤ ሀገርን አረንጓዴ ለማልበስ የተጀመረው መርሐ ግብር ላይ በመሳተፍ አሻራዋን በማኖሯ መደሰቷን ተናግራለች፡፡
ተፈጥሮን በመንከባከብ ንጹህ እና ውብ ከባቢን መፍጠር የሁሉም ሚና መሆኑን ጠቁማ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው መርሐ ግብር ለሌሎችም ምሳሌ የሚሆን ነው ብላለች፡፡
የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችን ጨምሮ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች እንደጀመሩት ሁሉ ለስኬታማነቱ መረባረብ እንዳለባቸውም ጠቁማለች፡፡
የቀበና ጤና ጣቢያ ሜዲካል ዳይሬክተር ታመነ መርክኝ በበኩላቸው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለጤናው ዘርፍ ስኬት ትልቅ አጋዥ ነው ብለዋል፡፡
ጤንነቱ የተረጋገጠ ትውልድ ለመፍጠር ብሎም ጽዱና ምቹ ከባቢን ከመገንባት አንጻር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡