የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ለተጀመሩ ስራዎች መሰረት የጣለ ነው-የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች

አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 22/2017(ኢዜአ)፦የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ለተጀመሩ ስራዎች መሰረት የጣለ  መሆኑን የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት ካሺም ሼቲማን፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳደሮች፣ የሁለቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች እንዲሁም ሚኒስትሮች በተገኙበት ትናንት በአዲስ አበባ የወንዝ ዳር ዳርቻ ልማት የችግኝ የተከላ መርሃ ግብር ተካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ የተገኙ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣  የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለጋራ ዓላማ በአንድነት መቆም ያለውን ውጤታማነት በተግባር የገለጠ ስለመሆኑ አብራርተዋል።

የሱማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሙስጠፌ መሀመድ፤ የክልሉ ነዋሪዎች በመርሃ ግብሩ ላይ በስፋት እየተሳተፉ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከዚህ ቀደም ለድርቅ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች ወደ ምርታማነት እንዲለወጡ እድል የፈጠረ መሆኑንም አብራርተዋል።

የተራቆቱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ በማድረግ የግብርና ምርታማነት እንዲሻሻል አዎንታዊ ሚና እያበረከተ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከዚህ አኳያ መርሃ ግብሩ በተደጋጋሚ በድርቅ ሲጎዳ ለነበረው የሱማሌ ክልል ልዩ ትርጉም እንዳለው አንስተው፤ በዘንድሮው ዓመትም የተሻለ ለውጥ ለማምጣት ሰፊ ተሳትፎ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳደር አወል አርባ በበኩላቸው፤ በክልሉ ከዚህ ቀደም በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተተከሉ የፍራፍሬ ተክሎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ መጀመራቸውን ጠቁመዋል።

ይህም የዜጎችን ገቢ በማሻሻል ረገድ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ መሆኑን አንስተዋል።


 

አሁን ላይ በክልሉ ችግኝ መትከል ባህል እየሆነ መምጣቱን አንስተው፤ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም ሰፊ ተሳትፎ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

በጋምቤላ ክልል በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አማካኝነት ከዚህ ቀደም በክልሉ የማይታወቁ አዳዲስ የፍራፍሬ ዓይነቶችን ማልማት መጀመሩን ያነሱት ደግሞ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ ናቸው።

ይህም በምግብ ራስን ለመቻል እና የህብረተሰቡን ገቢ ለመጨመር የተጀመሩ ጥረቶችን እያገዘ ስለመሆኑም ነው የተናገሩት።


 

የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ኦርዲን በድሪ፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከምግብ ሉዓላዊነት ጋር የተሳሰረ ሀገራዊ የልማት አጀንዳ መሆኑን አውስተዋል።

ህብረተሰቡ ያለ ልዩነት በጋራ እያደረገ ያለው ተሳትፎ ደግሞ መርሃ ግብሩ ውጤታማ እንዲሆን ትልቅ ሚና አበርክቷል ነው ያሉት።

  

"በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሃሳብ በሚካሄደው በዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች  ይተከላሉ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም