በኦሮሚያ ክልል በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚሰጡ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል

ክልል ፤ሰኔ 23/2017 (ኢዜአ) ፦ በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር  ዘርፈ ብዙ  ጥቅም የሚሰጡ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።

በክልሉ የዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር "በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ቃል በነገው እለት እንደሚጀመርም ተመላክቷል።

የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ የዘንድሮውን  የአረንጓዴ  አሻራ መርሃ ግብር ችግኝ ተከላ አስመልክቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ባለፉት ስድስት ዓመታት ከ6 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ላይ የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መተከላቸውን ጠቅሰው፣  ከተተከሉ  ችግኞች መካከል 88 በመቶ የሚሆኑት መጽደቃቸውን ተናግረዋል።

የአረንጓዴ ልማት ሥራው የውሃ አማራጮት እንዲሰፉ፣ በተፈጥሮ ሀብት መራቆት የደረቁ ሐይቆችና ወንዞች መልሰው እንዲያገግሙ ማድረጉንም ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈ  የአፈር መሸርሸርን በመቀነስ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ ማድረጉን ገልጸዋል።

ልማቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል በዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር  በበጋ ወራት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በተከናወነባቸው የተራቆቱ መሬቶች ችግኝ የመትከል ስራ እንደሚከናወን  ጠቅሰዋል።

ለዚህም በክልሉ በ38 ሺህ የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች ላይ ዘርፈ  ብዙ ጥቅም የሚሰጡ ችግኖች  መዘጋጀታቸውን አስታውሰዋል።

ችግኞቹን ለመትከል  1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት  መዘጋጀቱን ገልጸው፣  ለተከላ ከተዘጋጁት ችግኝ መካከል 40 በመቶው ለደን አገልግሎት የሚውሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም 30 በመቶ  የሚሆኑት ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያላቸው ፣ 19 በመቶ ለእንስሳት መኖ እና 10 በመቶው ለምግብ የሚውሉ  ሲሆን ቀሪው ለውበት እንደሚውሉ አቶ ጌቱ አስታውቀዋል።

የችግኝ ተከላ  መርሃ ግብሩን ስኬታማ ለማድረግ  ህዝቡ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ  በስፋት እንዲሳተፍም ጥሪ አቀርበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም