አረንጓዴ አሻራ የግብርና ምርታማነትን ከማሳደግ ጀምሮ በሁሉም የልማት መስኮች ተጨባጭ ውጤት አምጥቷል

 

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 23/2017(ኢዜአ)፦ አረንጓዴ አሻራ የግብርና ምርታማነትን ከማሳደግ ጀምሮ በሁሉም የልማት መስኮች ተጨባጭ ውጤት ማምጣቱን ሚኒስትሮች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፣ የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት ካሺም ሼቲማ፣ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር መካሄዱ ይታወቃል።

በመርሃ ግብሩ ከተሳተፉ ሚኒስትሮች መካከል አስተያየታቸውን የሰጡት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር)፥ ባለፉት ዓመታት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በሁሉም መስክ መሰረት መጣሉን ተናግረዋል።


 

የደን ሽፋንን በማሳደግ፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃን በማጎልበትና የግብርና ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ የወጪ ንግድ አቅምን ማስፋት ማስቻሉን ጠቅሰዋል።

በሁሉም የልማት መስኮች የኢኮኖሚ ዕድገትን በማፋጠን ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ኢትዮጵያ እንድታንሰራራ እያደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በዘንድሮው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በመሳተፍ የበኩሉን አሻራ እንዲያሳርፍም ጥሪ አቅርበዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው፥ አረንጓዴ አሻራ ጤናችን፣ ምግባችን እና ሁሉ ነገራችን ነው ብለዋል።

በአረንጓዴ አሻራ ለባህላዊና ዘመናዊ መድሃኒት የሚያገለግሉ ዕጽዋቶች እየተተከሉ መሆኑን ጠቅሰው፥ ይህም የመርሃ ግብሩን ሀገራዊ የጤና ዘርፍ ፋይዳ የላቀ ያደርገዋል ነው ያሉት።


 

መርሃ ግብሩ ምቹና አረንጓዴ አካባቢን በመገንባት ለህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ትልቅ ሚና እንዳለው ጠቅሰው፥ ሁሉም ህብረተሰብ በችግኝ ተከላው የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለበት ገልጸዋል።

የፍትሕ ሚኒስትር ሀና አርዓያ ሥላሴ፥ ኢትዮጵያውያን በአረንጓዴ ልማት አኩሪ የሆነ ባህል አለን ሲሉ ገልጸዋል።

ይህን መልካም ባህል ማስቀጠል እንደሚገባ በመግለጽ፥ ኢትዮጵያን አረንጓዴ በማልበስ ለመጪው ትውልድ የተሻለች ሀገር ለማስረከብ ሁሉም ጥረቱን ማጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል።


 

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ግብ ተይዟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም