በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ 3 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ ማልማት ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ 3 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ ማልማት ተችሏል

አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 22/2017(ኢዜአ)፦በሀገር አቀፍ ደረጃ በዘንድሮ በጋ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ከ3 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት ማልማት መቻሉን በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ፋኖሴ መኮንን ገለጹ።
መሪ ስራ አስፈፃሚው ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ በኢትዮጵያ የተጎሳቆለ መሬትና አካባቢን ለማከም መንግስት ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የአፈር ለምነት ማጣት፣ የአፈር መሸርሸር፣ የማህበረሰቡ የጎርፍ ተጋላጭነት መጨመር እና ሌሎች ተግዳሮቶችን ለመፍታት ህብረተሰቡን ያሳተፈ የተፈጥሮ ሀብት ጥብቃ ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎችም ወደ 33 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት እንዲያገግም መደረጉን ጠቅሰዋል።
በየዓመቱም እንደ አካባቢው ነባራዊ ሁኔታ ከ30 እስከ 60 ቀናት በሚቆዩ ጊዜያት ህብረተሰቡ በሚያደርገው የነቃ ተሳትፎ የሥነ አካላዊ፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ተግባር በልዩ ትኩረት መሰራቱን ገልጸዋል።
እየተገባደደ ባለው በጀት ዓመት ከ21 ሺህ በላይ በሚሆኑ ተፋሰሶች ላይ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።
በተፋሰስ ልማቱ ከ 3 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት መሸፈን መቻሉን ነው ያነሱት።
የተፈጥሮ ሀብት፣ የአፈርና ውሀ ጥበቃ እና የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት የአፈር ለምነትን እና ጤንነትን በመጠበቅ ትልቅ ለውጥ ማምጣቱን ገልጸዋል።
የአፈር መሸርሸርን በከፍተኛ መጠን መቀነሱን፣ የውሃ ሀብቶች እንዲጎለብቱ ማስቻሉን አንስተዋል።
አርሶ አደሮች የተቀናጀ የተፋሰስ ልማቱን በባለቤትነት በማልማት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በንብ ማነብና ሌሎችም ዘርፎች ተጠቃሚ እየሆኑ የግብርና ምርትና ምርታማነት እየጨመረ እንደሚገኝ ነው የጠቀሱት።
አቶ ፋኖሴ አያይዘውም በተፋሰስና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ መትከያ ጉድጓዶች እንዲዘጋጁ መደረጉን አንስተዋል።
የተፋሰስ ልማቱ ከአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ጋር በተሳሰረ መልኩ እየተተገበረ መሆኑም ሀገራዊ የአረንጓዴ ልማትና አካባቢ ጥበቃ ኢኒሼቲቭን እያሳካ ነው ብለዋል።