የበለጸገችና ጽዱ ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ሁሉም ዜጋ የአካባቢ ጥበቃ አምባሳደር መሆን አለበት - ኢዜአ አማርኛ
የበለጸገችና ጽዱ ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ሁሉም ዜጋ የአካባቢ ጥበቃ አምባሳደር መሆን አለበት

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 21/2017(ኢዜአ)፦ የበለጸገችና ጽዱ ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ሁሉም ዜጋ የአካባቢ ጥበቃ አምባሳደር መሆን እንደሚጠበቅበት የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ ገለጹ።
በመዲናዋ የ90 ቀን ልዩ የንቅናቄ አጀንዳ አካል የሆነው የፅዱ ኢትዮጵያ ከተማ አቀፍ ንቅናቄ "ፅዱ፣ ውብ እና ደህንነቷ የተጠበቀች አዲስ አበባ" በሚል መሪ ሀሳብ በይፋ ተጀምሯል።
የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ፤ የጠቅላይ ሚነስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የጽዱ ኢትዮጵያ ትልም ቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ሀገር እንዲረከብ የሚያስችል መሰረት መጣሉን ገልጸዋል።
በዚህም የኮሪደር፣ የወንዝ ዳርቻ ልማቶችና የመንግስት መስሪያ ቤቶች የስራ ከባቢ ጽዳትና የኢኮ-ቱሪዝም መዳረሻ ልማት ዜጎች የተሻለ የኑሮ ከባቢ እንዲኖራቸው እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
ባለፈው ዓመት በተካሄደው የመጀመሪያው የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ብክለትን በመግታት የተሻለ የኑሮ ከባቢን መፍጠር የሚያስችል የጽዳትና ውበት ስራ መሰራቱን አስታውሰዋል።
ባለስልጣኑም በህግ በተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት መሰረት ዜጎችን በንጹህና ጤናማ አካባቢ የመኖር መብታቸውን እውን ለማድረግ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዚህም የአፈር፣ የፕላስቲክ፣ የውሃ፣ የአየር፣ የድምጽ ብክለቶችንና የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማን መሰረት በማድረግ ጽዳትና ውበትን ባህሉ ያደረገ ዜጋ ለማፍራት መሰረት እየተጣለ መሆኑን አንስተዋል።
የአካባቢ ጽዳትና ውበት ጉዳይ የአንድ ተቋምና ግለሰብ ብቻ ሳይሆን የሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ትብብር ተሳትፎ የሚጠይቅ መሆን እንደሚኖርበት ገልጸዋል።
በብክለት ሳቢያ የሚደርሱ የጤና እክሎችን ቀድሞ በመከላከል የበለጸገችና ጽዱ ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ በሚደረገው ጥረት ሁሉም ዜጋ የአካባቢ ጥበቃ አምባሳደር መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ፤ በተያዘው የክረምት ወቅት በዘጠና ቀናት መዲናዋን እያፈኳት የሚገኙ የጽዳትና ውበት የበጎ አድራጎት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
በዚህም የጎርፍ አደጋን የመከላከል፣ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮች ጽዳት፣ ደረቅ ቆሻሻ ማስወገድን ጨምሮ ሌሎች ተግባራት እንደሚከናወኑ ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ድዳ ድሪባ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ባለፉት ዓመታት የመዲናዋን ጽዳትና ውበት በመጠበቅ ለጽዱ ኢትዮጵያ መሰረት የሆኑ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ተሰርተዋል።
የኮሪደርና የወንዝ ዳር ልማት እንዲሁም የመልሶ ልማት ስራዎችም ፋይዳቸው የላቀ መሆኑን ጠቅሰው፥ የወንዞችን ብክለት መከላከል የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ ተቀርፆ ስራ ላይ ማዋል እንደተቻለም ገልጸዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሃ ግብርም ለአካባቢ ፅዳትና ውበት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የፌዴራል፣ የከተማ አስተዳደሩና የዓለም አቀፍ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች፣ የሲቪክ ማህበራት ተወካዮች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና የኪነ-ጥበብ ሙያተኞች ተገኝተዋል።