ቀጥታ፡

ለብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን አከባበር በመሰረተ ልማት አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ነው - የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር

ሆሳዕና፤ ህዳር 5/2018(ኢዜአ)፦ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሆሳዕና ከተማ ለሚከበረው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በመሰረተ ልማት አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።

20ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን "ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለሀብረብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ ይከበራል።

በዓሉ በፌደራል ደረጃ በሚከበርበት ሆሳዕና ከተማ ከማክበሪያ ስፍራና እንግዶች ማረፊያ ጀምሮ የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው።

በዝግጅት ምዕራፍ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል የመሰረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች በዋናነት ይጠቀሳሉ።


 

የሆሳዕና ከተማ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ዕህፈት ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ተከተል ጩፋሞ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በከተማው በፌዴራልና በከተማ አስተዳደሩ ከ30 ኪሎ ሜትር በላይ የአስፓልት መንገድ ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡

በከተማ አስተዳደሩ በመጀመሪያ ምዕራፍ የ12 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ሥራ እየተከናወነና ልማቱ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ 

ከተማዋን ተወዳዳሪና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ የሚገነቡ የመሰረተ ልማት ሥራዎች የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ቀን በዓልን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እየተከናወኑ መሆኑንም ገልጸዋል።

በተለይ የመንገድ መሰረተ ልማቱን ከበዓሉ አስቀድሞ ለማጠናቀቅ ትኩረት መሰጠቱን ነው ያመለከቱት።


 

በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የሶዶና አካባቢው ፕሮጀክቶች ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሰለሞን ሞላ በበኩላቸው እንዳሉት ተቋሙ በራሱ ወጪ በከተማው የ10 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ሥራ ያከናውናል።

የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ አካል የሆነው የ4 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ሥራን በተያዘው ወር መጨረሻ በማጠናቀቅ ለበዓሉ ለማድረስ ርብርብ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። 

የኮሪደር ልማቱ ሥራው የተሽከርካሪና የእግረኛ መንገዶችን ጨምሮ የመዝናኛ፣ የአረንጓዴ ስፍራዎች፣ የመንገድ አካፋይና መብራቶችን ባካተተ መልኩ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡


 

የመሳይ ኦሊ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ የሆሳዕና ከተማ ኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ታደሰ አማኑኤል በበኩላቸው፣ ልማቱን በታቀደው ጊዜ ለማጠናቀቅ ቀንና ማታ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የኮሪደር ልማት ሥራውን ለኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ለማድረስ በርብርብ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።


 

በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ከተማዋን ለነዋሪው ምቹ ከማድረግ ባለፈ ከአቻ ከተሞች ጋር ተወዳዳሪ የሚያደርጋት ነው ያሉት ደግሞ የከተማው ነዋሪ እሸቱ ኃይሌ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በከተማው መከበር የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ከማጠናከር ባለፈ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም