በሰሜን ወሎ ዞን በሚገኙ ሶስት ከተሞች የኮሪደር ልማት ስራ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሰሜን ወሎ ዞን በሚገኙ ሶስት ከተሞች የኮሪደር ልማት ስራ እየተከናወነ ነው
ወልዲያ ፤ሕዳር 5/2018 (ኢዜአ)፡-በሰሜን ወሎ ዞን ሶስት ከተሞች የኮሪደር ልማት እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ከተሞችና መሠረተ ልማት መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ኃላፊ አቶ መኮንን የሱፍ ለኢዜአ እንደገለጹት የኮሪደር ልማት ስራው እየተከናወነባቸው የሚገኙት የቆቦ፣ የመርሳና የጋሸና ከተሞች ናቸው።
በሶሰቱም ከተሞች የ11 ኪሎ ሜትር የአስፋልት፣ የእግረኛ፣ የሳይክልና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ያሟላ የኮሪደር ልማት እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የውሃ ማፋሰሻ ቦዮች፣ ድልድዮችን፣ ደረጃውን የጠበቀ የመንገድ መብራት፣ የመዝናኛ ስፍራዎች፣ የአረንጓዴ ልማትና ሌሎች መሰረተ ልማትን አካቶ እንደሚገነባ ተናግረዋል።
አሁን ላይ የግንባታ አካባቢዎችን የማጽዳት፣ የቁፋሮና አፈር ቆረጣ እንዲሁም የገረጋንቲ ሙሌት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው በዚህም ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል ተፈጥሯል ብለዋል።
የኮሪደር ልማቱ እየተከናወነ የሚገኘውም ከከተሞቹ መስተዳድሮች፣ ከነዋሪዎችና ባለሃብቶች በሚሰበሰብ ከ950 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ መሆኑን ገልጸዋል።
በሃምሌ ወር 2017 ዓ.ም የተጀመረው የኮሪደር ልማት አሁን ላይ አፈጻጸሙ 25 በመቶ መድረሱን ጠቁመው በያዝነው በጀት ዓመት መጨረሻ ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
የቆቦ ከተማ ነዋሪው አቶ ወንድምነው ሞላ በሰጡት አስተያየት ከተማችንን ለማስዋብና ደረጃዋን የጠበቀች ለማድረግ ከመስተዳድሩ ጋር በመተባበር የኮሪደር ልማቱን እያካሄድን እንገኛለን ብለዋል።
መስተዳድሩ ከህብረተሰቡ ጋር ባካሄደው ውይይት የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ስራው እየተከናወነ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የመርሳ ከተማ ህዝብ አሸዋና ድንጋይ በማቅረብ፣ ገንዘብ በማዋጣትና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ ለኮሪደር ልማቱ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የከተማዋ ነዋሪ አቶ አህመድ የሱፍ ናቸው።
በሌሎች ከተሞች የተከናወኑ የኮሪደር ልማት ስራዎች በቁጭት እንድንነሳ አድርጎናል ሲሉም ተናግረዋል።