ቀጥታ፡

የባሌ ዞን የቱሪስት መዳረሻዎች ልማት የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር አድርጓል

ሮቤ፤ ህዳር 5/2018(ኢዜአ)፦ በባሌ ዞን የቱሪስት መዳረሻዎችን ለማልማትና ለማስተዋወቅ የተሰሩ ተግባራት የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር ማድረጋቸውን የዞኑ ቱሪዝም ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

በቱሪስቶች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተሰማሩ ነዋሪዎችና ማህበራትም ከዘርፉ ተጠቃሚነታቸው ማደጉን ገልጸዋል።

በጽህፈት ቤቱ የቱሪዝም ልማትና ማስፋፊያ ቡድን መሪ ሽብሩ አብዶ ለኢዜአ እንደተናገሩት የዞኑን የቱሪስት መስህቦች በማልማትና በማስተዋወቅ የዘርፉን አኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማሳደግ እየተሰራ ነው።


 

ይህም ዞኑን የሚጎበኙ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ቱሪስቶች ቁጥር እንዲጨምር በማድረጉ በበጀት አመቱ የመጀመሪያው ሩብ አመት 16ሺህ 217 ቱሪስቶች መዳረሻዎቹን ጎብኝተዋል ብለዋል፡፡

መስህቦቹን የጎበኙት ቱሪስቶች ቁጥር ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወራት ጋር ሲነጻጸር በ15 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን አመልክተዋል።

የቱሪስት መዳረሻ ልማቱ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ከማሳደግ ባለፈ የአካባቢውን ባህል ለማስተዋወቅና በዘርፉ ለተሰማሩ አካላት ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አክለዋል።


 

ለአብነትም በሩብ አመቱ አካባቢውን ከጎበኙ ቱሪስቶች ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን በማሳያነት አንስተዋል።

ለቱሪስቶች ቁጥር መጨመር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በአካባቢው እየተከናወኑ ያሉ መሰረተ ልማቶች እና አካባቢውን ለማስተዋወቅ የተደረጉ የተቀናጁ ጥረቶች እና የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በዩኔስኮ በቋሚ ቅርስነት መመዝገብ ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።

በቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መካከል በሮቤ ከተማ የቱሉ ሀምበላት የባህል ልብስ ቤት ተወካይ ወይዘሮ መርየማ ከድር ባሌ ሮቤን ለሚጎበኙ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ቱሪስቶች የባህል አልባሳት እንደሚሸጡ ተናግረዋል።

የቱሪስቶች ቁጥር መጨመርና በተለያዩ ዲዛይኖች የሚያዘጋጁት የባህል አልባሳት ጥራት በሥራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ማገዙን አስረድተዋል።

የባሌ ፓርክን በአስጎብኚነትና በመንገድ በመምራት አገልግሎት የተሰማራው የዋሊያ ኢኮ-ቱሪዝም ማህበር ስራ አስኪያጅ ጃፈር መሐመድ በበኩሉ ፓርኩን ለማልማት የተደረገውን ጥረት ተከትሎ የጎብኚዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።

ይህም የማህበሩ አባላትም መንገድ በመምራት፣ ፈረስ በማከራየት የሚያገኙት ገቢ እንዲጨምር ማድረጉን ተናግረዋል።

በባሌ ዞን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት/ዩኔስኮ/ በአለም የተፈጥሮ ቅርስነት የተመዘገበውን የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን ጨምሮ ሌሎች ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ መስህቦች ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም