የገጠር አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እያገዙ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የገጠር አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እያገዙ ነው
ድሬዳዋ፣ ህዳር 5/2018(ኢዜአ) በድርዳዋ የገጠር አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ማገዛቸውን የአስተዳደሩ ግብርና ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ በሚሆን በጀት በአራቱም የገጠር ክላስተሮች የአነስተኛ መስኖና የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታ እያፋጠነ መሆኑን አመልክቷል።
በቢሮው የውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፉአድ መሐመድ ለኢዜአ እንዳስታወቁት፥ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ አስተዳደሩ የገጠሩን ማህበረሰብ የልማት ጥያቄዎች በመመለስ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ ይገኛል።
በዚህም በአነስተኛ መስኖ ፕሮጀክቶች ሲለማ የነበረን ማሳ ከ4 ሺህ 500 ሄክታር ወደ 8ሺህ 500 በማሳደግ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል።
እነዚህን ውጤቶች ለማስፋት ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ በጀት በመመደብ በአራቱም የአስተዳደሩ ገጠር ክላስተሮች የመጠጥ እና የአነስተኛ መስኖ ፕሮጀክቶች መፋጠናቸውን አክለዋል።
ለአብነት በአሰሊሶ ክላስተር በ153 ሚሊዮን ብር የተገነባው በፀሐይ ኃይል የሚሰራው የመጠጥ እና የአነስተኛ መስኖ ፕሮጀክት የአካባቢውን አርሶአደሮች ተጠቃሚ ማድረጉን አንስተዋል።
ሌሎች በከፊል አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት የመስኖ ፕሮጀክቶችም 500 ሄክታር መሬትን በመስኖ ማልማት ማስቻላቸውን ተናግረዋል።
እንደ አቶ ፉአድ ገለፃ፥ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ አስተዳደሩ ለገጠሩ ማህበረሰብ በሰጠው ትኩረት በተሰሩት የልማት ስራዎች የገጠር ቀበሌዎች የመጠጥ ውሃ እና 33ቱ ደግሞ የአነስተኛ መስኖ ተጠቃሚ ሆነዋል።
የገጠሩ ማህበረሰብ ፕሮጀክቶችን በባለቤትነት ከመንከባከብ በተጨማሪ በቡድን እየተደራጀ በጉልበቱ እና በገንዘቡ ለመስኖ የሚጠቀምበትን የውሃ ጉድጓዶች በመቆፈር ፀጋዎቹን ወደ ልማት እያሻገረ መሆኑንም ተናግረዋል።
በገጠሩ ማህበረሰብ ትጋት ከተረጂነት ሙሉ በሙሉ ለመላቀቅና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ኃላፊው ተናግረዋል።
የድሬዳዋ ገጠር ክላስተሮች የአስተዳደሩን 96 ከመቶ በላይ የቆዳ ስፋትና አንድ ሶስተኛውን ህዝብ ያካተተ ቢሆንም መልክዓ ምድሩ ዝናብ አጠርና በረሃማ መሆኑን ተከትሎ ባለፉት ጊዜያት ማህበረሰቡ ለተረጂነት ሲጋለጥ መቆየቱ ይታወሳል።
በአሁኑ ጊዜ ማህበረሰቡ ተረጂነትን በፍጥነት ወደ ታሪክ ለመቀየር እያደረገ የሚገኘው ትጋት ውጤት እያስገኘ መሆኑንም ነው የገለጹት።