በጅማ ከተማ ስምንት የቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎችን በማቋቋም የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጅማ ከተማ ስምንት የቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎችን በማቋቋም የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እየተሰራ ነው
ጅማ፤ ህዳር 5/2018(ኢዜአ)፦ በጅማ ከተማ ስምንት የቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎችን በማቋቋም የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እየተሰራ መሆኑን የከተማው ንግድ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የከተማው ንግድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ጉተማ ጊዲ ለኢዜአ እንዳሉት በከተማው የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የሚያግዙ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ ነው።
በተለይም የቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎችን በማስፋፋት የምርት አቅርቦትና ተደራሸነት እንዲጠናከር የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም በከተማው ስምንት የቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎች ተደራጅተው ምርቶች፣ ሸቀጦችና ሌሎች የፍጆታ እቃዎች ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይ ገበያዎቹ አምራች እና ሸማቹን ስለሚያገናኙ በህገ ወጥ ነጋዴዎች የሚፈጠረውን ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረት ለመከላከል እያገዙ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም በሸማች ህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት ሸቀጦችና ምርቶች ለህብረተሰቡ እንዲቀርቡ እየተደረገ መሆኑንም አውስተዋል።
ከዚህ ጎን ለጎንም በህገ ወጥ ንግድ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎችና የንግድ ተቋማት ላይ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አስረድተዋል።
በተለይም ያለበቂ ምክንያት ዋጋ በሚጨምሩና ምርት በሚደብቁ ነጋዴዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃዎች እየተወሰደ እንደሆነ ጠቁመው እርምጃው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በተሰራው ስራ በከተማዋ የተረጋጋ የግብይት ሁኔታ መኖሩን አመልክተው ከአምራቾችና ከጅምላ ነጋዴዎች ጋር በመቀናጀት የምርት አቅርቦት ስራው ይጠናከራል ነው ያሉት።
በከተማው ከሚገኙ የሸማች ህብረት ስራ ማህበራት መካከል የጊንጆ ጉዱሩ ማህበር ሊቀመንበር ኦላኒ ቀልቤሳ፣ በማህበሩ የተለያዩ ምርቶችና ሸቀጦችን ለሸማቹ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎና ሌሎች የግብርና ምርቶችን ጨምሮ ስኳርና ዘይት እያቀረቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ከከተማው ነዋሪዎች መካከል ኤሊያስ አባጀበል፣ በከተማዋ የተጀመረው ገበያን የማረጋጋት ስራ ውጤታማ በመሆኑ መጠናከር አለበት ብለዋል።
አሁንም ያለበቂ ምክንያት ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ መጠናከር እንዳለበትም ጠቁመዋል።
በከተማው በተቋቋሙ የቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎች የምርት አቅርቦቱ የተሻለ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላው የከተማው ነዋሪ አብዱል ባሲጥ አባ ገሮ ናቸው።
በአንዳንድ ነጋዴዎች ላይ የተጀመረው ክትትልም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።