ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የማስገንዘብ ስራዎች እየተሰሩ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 6/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚያስገነዝቡ የዲፕሎማሲ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ገለጹ።

በዚምባብዌ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደርና በሞሪሽየስ፣ በዛምቢያ፣ በምስራቅና ደቡብ አፍሪካ አገራት የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) የኢትዮጵያ ተጠሪ ረሺድ መሀመድ፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር ያጣችበት መንገድ በፖለቲካ አሻጥር የተሸረበ ኢ-ፍትሕዊ ውሳኔ እንደነበር አስታውሰዋል።

ትልቅ የህዝብ ቁጥር ያላት ኢትዮጵያ የባሕር በር ተዘግቶባት ልትኖር እንደማትችል የቀረበው ፍትሕዊ ጥያቄም ዓለም አቀፍ ሕግ የሚደግፈው መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነትም የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናን ሰላምና ደኅንነት በማስጠበቅ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ አጀንዳ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን ተፈጥራዊና ታሪካዊ ባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄም በዚምባብዌና ዛምቢያ ለሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት የማስገንዝብ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል።

በኩዌት የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሰኢድ መሀመድ(ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ፍትሕዊ ተጠቃሚነትን የማስጠበቅ የህልውና ጉዳይ ነው ብለዋል።

በዚህም የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በሁሉም አማራጭ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የማስገንዘብ ሚናቸውን እንዲወጡ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው በጋራ ተጠቃሚነት ዲፕሎማሲያዊ መርህ የቀረበ ጥያቄ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

በእንግሊዝ እና ሰሜን አየርላንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብሩክ መኮንን ዳያስፖራው ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ ይደርስባት የነበረውን ጫና በመቋቋም ረገድ ቀዳሚ ሚና መወጣቱን አውስተዋል።

ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የባህር በር ጥያቄን ተገቢነትና ፍትሃዊነት በማስረዳትም በኩል የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ኤምባሲው ዳያስፖራው በተለያዩ አማራጮች የኢትዮጵያን አቋም ተገቢነትና ፍትሃዊነት በማስረዳት እያደረገ ያለውን ድጋፍ ለማጠናከር እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የባህር በር ያጣነው ህጋዊ ባልሆነ መንገድና በተሳሳተ ፖሊሲ ነው ያሉት ደግሞ በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በሚኒስትር ደረጃ የዳያስፖራ ዘርፍ ዲፕሎማት መላኩ ዘለቀ ናቸው።

ዳያስፖራው ከዚህ ቀደምም የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የማሳወቅ ሚናውን ሲወጣ መቆየቱን ጠቅሰው፤ የባህር በር ጥያቄንም በማስረዳት በኩል ሚናውን እንደሚወጣ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም