በጉጂ ዞን በአትክልት ልማት የተሰማሩ ነዋሪዎች ተጠቃሚ እየሆኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጉጂ ዞን በአትክልት ልማት የተሰማሩ ነዋሪዎች ተጠቃሚ እየሆኑ ነው
አዶላ ፤ሕዳር 5/2018 (ኢዜአ)፡-በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በአትክልት ልማት የተሰማሩ ነዋሪዎች ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱን ገለጹ።
በዞኑ በአነስተኛ የመስኖ ልማት ተሰማርተው የምግብ ዋስትናቸውን እያረጋገጡ ካሉ የአዶላ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ምህረት ይልማ፤ ባለፉት አራት አመታት ሰላጣ፣ ጎመን፣ ቆስጣ፣ ቃሪያና ፓፓያ ማልማታቸውን ገልጸዋል፡፡
የመስኖ ልማት ስራቸው ውጤታማ በመሆኑም ከጉጂ ዞንና ከአዶላ ከተማ አስተዳደር የእውቅና ሽልማት ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
ሽልማቱ በፈጠረላቸው መነሳሳት ጠንክረው በመስራት በአትክልትና ስራስር ልማቱ ገቢያቸውን ማሳደግ መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡
የጀመሩት አነስተኛ የመስኖ ልማት የተመጣጠነ ምግብን ከማግኘት ባለፈ ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ማሳደግ እንደቻሉ ጠቁመዋል፡፡
የአዶላ ወረዳ ነዋሪው አቶ ጀማል ጉራቻ በበኩላቸው፤ ፓፓያ፣ ድንች፣ ቲማቲምና ቀይ ሽንኩርት በማምረት ለገበያ አቅርበው ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የመስኖ ልማት በትንሽ መሬት ላይ ብዙ በማምረት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንዳገዛቸው ገልጸው ለሌሎች አርሶ አደሮች ልምዳቸውን ማካፈላቸውን ተናግረዋል፡፡
የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ መንግስቱ ሂርባዬ እንዳሉት፤ በዞኑ በአነስተኛ መስኖ የአትክልት ልማት ስራ ከ25 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች እየተሳተፉ ነው፡፡
ልማቱም የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ከሚያበረክተው ፋይዳ ባለፈ ገበያን ለማረጋጋት የራሱን ድርሻ ማበርከቱን አክለዋል።
የመስኖ ልማቱን ውጤታማ ለማድረግ የግብአት አቅርቦትና የግብርና ባለሞያዎች ክትትል እንዲሁም ለአርሶ አደሮች ግንዛቤ መሰጠቱን ገልጸዋል።
በዚህም ድንች፣ ቀይ ሽንኩርት፣ ጥቅል ጎመን፣ ካሮት፣ ቀይስር፡፤ ቲማቲም፣ ቃሪያ፣ ሙዝና ፓፓያ በስፋት እየለማ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡