በከብት ማድለብ ስራ ላይ የተሰማሩ አርሶአደሮች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በከብት ማድለብ ስራ ላይ የተሰማሩ አርሶአደሮች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ ነው
መቱ፤ሕዳር 5/2018 (ኢዜአ)፡- በከብት ማድለብ ስራ በመሰማራት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መሆናቸውን በኢሉባቦር ዞን የበቾ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።
ነዋሪዎቹ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በከብት ማድለብ ስራ በመሰማራት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ ነው።
በበቾ ወረዳ የጉዲና ቀበሌ ነዋሪው አቶ አያና አደም በመንግስት የተቀረፁ የግብርና ልማት ፕሮግራሞችን በመተግበር የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ መቻላቸውን ተናግረዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን በከብት ማድለብ ስራ በመሰማራት ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ለማሳደግ በሚያደርጉት ጥረት በዓመት ከ50 እስከ 60 በሬዎችን አደልበው ለገበያ በማቅረብ ተጨማሪ ገቢ ማግኘታቸውን ጠቅሰዋል።
በዚሁ ወረዳ የጉዲና ሶር ቀበሌ ነዋሪዎቹ አቶ አብዲሳ ሆማ እና አቶ በላቸው ሆማ በበኩላቸው መንግስት በፈጠረላቸው ግንዛቤ በከብት ማድለብ ስራ ተሰማርተው ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የመኖ አቅርቦቱን ከግብርና ስራቸው ጋር በማስተሳሰር ያደለቧቸውን ከብቶች በዓመት እስከ ሶስትና አራት ዙሮች ለገበያ ማቅረባቸውን አውስተዋል።
በዚህም ጥሩ ገቢ በማግኘት የኢኮኖሚ አቅማቸውን በማሳደግ ሰባት ሚሊዮን ብር ካፒታል በማፍራት ወደ ኢንቨስትመንት እንደተሸጋገሩ ገልጸዋል።
የኢሉባቦር ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አወል መሐመድ በበኩላቸው፤ በዞኑ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚሆኑ የዳልጋ ከብቶች መኖራቸውን ጠቁመው ከዞኑ የእንስሳት ሀብት ተጠቃሚ ለመሆን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የእንስሳቱን ምርታማነት ከማሳደግ ባለፈ የመኖ አቅርቦትና አርሶ አደሩ ከብቶችን አደልቦ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚነቱን ለማሳደግ የቅርብ ክትትል መደረጉን አንስተዋል።
በዚህም አርሶ አደሩ በየዓመቱ ከ240 ሺህ በላይ ከብቶችን አድልቦ ለገበያ በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ማሳደጉን ተናግረዋል።
በከብት ማድለብ ስራው በመሳተፍም በርካታ አርሶ አደሮች የኢኮኖሚ አቅማቸው ከማሳደግ አልፈው ሀብት በማፍራት ወደ ኢንቨስትመንት መሸጋገር መቻላቸውን አስረድተዋል።