በጋምቤላ ከተማ የተጀመረው የኮሪደር ልማት እየተፋጠነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ከተማ የተጀመረው የኮሪደር ልማት እየተፋጠነ ነው
ጋምቤላ፤ ሕዳር 5/2018 (ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ከተማ የተጀመረውን የኮሪደር ልማት በፍጥነት በማጠናቀቅ ከተማዋን ለነዋሪዎቿ የተመቸችና የቱሪዝም መስህብ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።
የጋምቤላ ከተማ ለቱሪስት መዳረሻ በሚሆኑ የተፈጥሮ ፀጋዎች ተከባ የምትገኝ ሲሆን፤ በተለይም ከተማዋን ለሁለት ከፍሎ የሚያልፈው የባሮ ወንዝ ለከተማዋ ልዩ ውበትና ድምቀት የሚያጎናጽፍ እንደሆነ ተመልክቷል።
የከተማዋ አስተዳደር ከንቲባ ቱት ጂክ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የጋምቤላን ውበትና ፀጋን ይበልጥ ለማጉላት እንደ ሀገር የተጀመረው የኮሪደር ልማት ኢኒሼቲቨ በከተማዋም እየተተገበረ ይገኛል።
በጋምቤላ ከተማ የተጀመረውን የኮሪደር ልማት በማፋጠን ከተማዋን ለነዋሪውና ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ እየተከናወነ ያለው ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡
በከተማው በመጀመሪያው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ከ14 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸው አራት ዋና ዋና መንገዶችን ለማልማት የተያዘውን ግብ ለማሳካት ስራው በመፋጠን ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
ነዋሪውም ለኮሪደር ልማቱ ስኬታማነት ሀብት ከማሰባሰብ ጀምሮ እያሳየ ያለው ትብብር እና ድጋፍ የሚደነቅ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ከኮሪደር ልማቱ ጎን ለጎን የከተማውን የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ደረጃ በማሻሻል የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
የተጀመረው የኮሪደር ልማት ከተማዋን ጽዱ፣ ውብና ማራኪ ከማድረግ ባለፈ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል እየፈጠረ መሆኑንም ከንቲባው አስታውቀዋል፡፡
በኮሪደር ልማቱ የስራ እድል ከተፈጠረላቸው መካከል ወጣት አጥናፉ አሰፋ ፤ የኮሪደር ልማቱ በፈጠረለት የስራ እድል ራሱንና የቤተሰቦቹን ህይወት መቀየሩን ነው የተናገረው።
የኮሪደር ልማቱ ከተማውን ይበልጥ ውብና ሳቢ ከማድረግ ባለፈ አዳዲስ ሙያዎችን እንዲለምዱ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸውም ወጣቶቹ ገልጸዋል።