በደብረ ብርሃን ከተማ ለአምራች ኢንዱስትሪ ምቹ የኢንቨስትመንት ምኅዳር ተፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
በደብረ ብርሃን ከተማ ለአምራች ኢንዱስትሪ ምቹ የኢንቨስትመንት ምኅዳር ተፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ሕዳር 5/2018 (ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ለአምራች ኢንዱስትሪ የተፈጠረው ምቹ ምኅዳር ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው በደብረብርሃን ከተማ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ አምራቾች ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞንና ደብረ ብርሃን ከተማ በአምራች ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ድርጅቶችን መጎኘታቸው ይታወሳል።
በዚሁ ወቅትም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በደብረ ብርሃን ከተማ የተገነባውን የብራውን ፉድ የብቅልና አልሚ ምግብ ማምረቻ ፋብሪካ መርቀው ስራ አስጀምረዋል።
የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰሜን ሸዋ ዞንና ደብረ ብርሃን ከተማ የአምራች ኢንዱስትሪዎች የመስክ ምልከታ የምርታማነትን ለማሳደግ መነሳሳትን እንደሚፈጥር የድርጅት ስራ አስኪያጆች ገለጸዋል።
በበላይነህ ክንዴ ቢዝነስ ግሩፕ የፊቤላ ደብረ ብረሃን መኪና መገጣጠሚያ ስራ አስኪያጅ መሐመድ አሕመድ፥ የደረቅና ፈሳሽ ጭነት እንዲሁም በኤሌክትሪክ የሚሰሩ የከተማ ባሶችን እየገጣጠሙ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በቀን አስራ ሁለት፤ በዓመት 1 ሺህ ተሽከርካሪ የማምረት አቅም ያለው የፊቤላ ደብረ ብርሃን መኪና መገጣጠሚያ የነዳጅ ወጪን በማስቀረት ለትራንስፖርት ዘርፍ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ ነው ብለዋል።
ዓለም የደረሰበትን ቴክኖሎጂን በመጠቀም ጥራት ያላቸው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እየተመረቱ ነው ብለዋል።
በመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካው የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ዜጎችም በቴክኖሎጂ የዕውቀትና ክህሎት ሽግግር ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የዴዴቦ ቦትል ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ ደሳለኝ ፈንታ፥ ብርጭቆ፣የምግብ ማሸጊያ ጃር፣ የለስላሳና የቢራ ጠርሙሶችን ለማምረት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
በቀን ከ450 ሺህ እስከ 500 ሺህ ጠርሙስ የማምረት አቅም ያለው ፋብሪካው 86 ከመቶ የሀገር ውስጥ ጥሬ ዕቃን በመጠቀም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ፋብሪካው ወደ ስራ ሲገባ በ24 ሰዓት የምርት ሂደት በርካታ ዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።
የደብረ ብርሃ ከተማ ለአምራች ኢንዱስትሪ ያላት ምቹ ምኅዳርና የተደረገላቸው የሚገኙ ድጋፍ በኢንቨስትመንት የሚሰማሩበትን ዕድል እንደፈጠረላቸው አስረድተዋል።