ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የማዕድን ጸጋዎችን ለማልማት ወሳኝ አቅም ፈጥሯል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 5/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የማዕድን ጸጋዎችን ለማልማት ወሳኝ አቅም መፍጠሩን በ4ኛው ዓለም አቀፍ የማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ ተሳታፊ አልሚዎች ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ 4ኛውን ዓለም አቀፍ የማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ(MINTEX Ethiopia 2025) በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መርቀው ከፍተዋል።

ከኅዳር 4 እስከ 7/2018 ዓ.ም በሚቆየው ኤክስፖ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሀገር ውስጥና የውጭ አልሚ ባለሃብቶችን፣ ቴክኖሎጂ አምራቾች፣ ምሁራን እና አጋሮች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

የኤክስፖው ተሳታፊ የሀገር ውስጥና የውጭ አልሚዎች ለኢዜአ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፍ የኢንቨስትመንት አቅምን ለማስፋት አበረታች የልማት ምኅዳር መፈጠሩን ገልጸዋል።

የአኮቦ ሚኒራልስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጆርገን ኤቭጀን፤ የማዕድን ኤክስፖው ምርትና አገልግሎታቸውን በማስተዋወቅ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ለማዕድን ዘርፍ የኢንቨስትመንት ከባቢ የፈጠረው የማበረታቻ ምኅዳር የወርቅ ማዕድን ልማት ስራን ለማስፋት አቅም እየፈጠረላቸው እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ሌላኛው የጂ.ሲ.ኤል ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሊ ጂያንጁን በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ የተፈጠረው ምቹ የኢንቨስትመንት ምኅዳር ሀገሪቱን ተመራጭ የልማት መዳረሻ እያደረጋት ነው ብለዋል።

ድርጅታቸው በኢትዮጵያ ከአሥር ዓመታት በላይ ያደረገው የነዳጅ ፍለጋ ፍሬ አፍርቶ የተፈጥሮ ጋዝ በማስመረቅ ሁለተኛውን ምዕራፍ ግንባታ እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ማዕድን ሃብት ጸጋዎችና ምቹ ኢንቨስትመንት መዳረሻነትን በመጠቀም ግዙፉ የድፍድፍ ነዳጅ ማጣሪያ ግንባታ ላይ እንዲገቡ ማስቻሉን ተናግረዋል።

በቀጣይም የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ምርት ልማት አቅምን በማሳደግ ኢትዮጵያን የኃይል አቅርቦት ማዕከል ለማድረግ በትጋት እንደሚሰሩ አስረድተዋል።

የኢምራን ጂምስቶን ዋና ዳይሬክተር ቢኒያሚን አቡበከር፤ የኢትዮጵያ መንግስት ለሀገር ውስጥና ለውጭ ባለሃብቶች የሚሰጠው ድጋፍ በማዕድን ልማት ከፍተኛ መነቃቃት እየፈጠረ ነው ብለዋል።

ለማዕድን አልሚዎች የተፈጠረው ምቹ የኢንቨስትመንት ምኅዳር ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የማዕድን ፍለጋ ልማት ስራን የሚያከናወኑበት ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።

በማዕድን ልማት ለተሰማሩ አልሚዎች የሚሰጠው የፋይናንስ አቅርቦት ከፍተኛ ዕድገት እያስመዘገበ ነው ያሉት ደግሞ በዳሸን ባንክ የማርኬቲንግ ክፍል የሽያጭ ኃላፊ ነጋ ሽባባው ናቸው።

በቀጣይም የኢትዮጵያን የማዕድን ሃብት ልማት ለማጠናከር የከበሩ ማዕድናት ካዝናን ጨምሮ የውጭ ምንዛሬ የገንዘብ አቅርቦት የማመቻቸት ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም