ቀጥታ፡

የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር አስችለዋል

አዲስ አበባ፤ሕዳር 5/2018 (ኢዜአ)፡-ባለፉት ዓመታት ህዝብን በማሳተፍ የተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የአፈር ለምነትን በማሳደግ ምርት እና ምርታማነት እንዲጨምር ማስቻሉን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ለዘንድሮ በጋ ተፋሰስ አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ እየተጠናቀቀ መሆኑም ተገልጿል።

የአየር ንብረት ለውጥ፣ ጎርፍ፣ የዝናብ መዛባት፣ ድርቅና የአፈር መሸርሸር የስነ ምህዳር መጓደል በማስከተል የሰውን ልጅ ለከፋ ጉዳት ይዳርጋሉ፡፡ 

ችግኝ መትከል፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ማከናወን ደግሞ የተፈጥሮን ስነ ምህዳር በማስተካከል የሰውን ልጅ ከከፋ ጉዳት ለመጠበቅ ያስችላል፡፡


 

በኢትዮጵያ በመከናወን ላይ የሚገኙት የአረንጓዴ አሻር መርኃ ግብርና የበጋ የተፋስስ ልማት ስራዎች ሀገሪቱ ለአካባቢ ጥበቃ የሰጠችውን ከፍተኛ ትኩረት የሚያሳዩ ናቸው፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ፋኖሴ መኮንን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ የተፈጥሮ ሃብት ከሰው ልጅ ኑሮ ጋር ከፍተኛ ቁርኝት አለው ብለዋል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ፣ ጎርፍ፣ ድርቅና የአፈር መሸርሸር የሚከሰተው ሰዎች በተፈጥሮ ላይ ለሚያደርሱት ጉዳት በሚሰጥ የተፈጥሮ ምላሽ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ 


 

ባለፉት ዓመታት ህዝብን በማሳተፍ በተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የአፈር ለምነትን በማሳደግ ምርት እና ምርታማነት እንዲጨምር ማስቻሉን ገልጸዋል።

በሀገሪቱ 135 ገባሮች (ሳብ ቤዝን) ያሏቸው 12 ትላልቅ (ቤዝን) ተፋሰሶች መኖራቸውን የጠቀሱት መሪ ስራ አስፈጻሚው፤ አሁን ላይ ተጨማሪ 8 ሺህ 903 ታላላቅ ተፋሰሶች ተለይተው በመልማት ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡ 

በማህበረሰብ ደረጃ ተለይተው በመልማት ላይ በሚገኙ 197 ሺህ 843 አነስተኛ ተፋሰሶች በየዓመቱ ስነ አካላዊና ስነ ህይወታዊ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡


 

በዚህም በመንግስትና በህብረተሰብ ተሳትፎ 33 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ መልሶ የማልማት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

የበጋ የተፋሰስ ስራ የሚከናወንባቸው ቦታዎችን፣ ቀያሽ አርሶ አደሮችና ለስራው የሚያገለግሉ የእርሻ መሳሪያዎችን የመለየት ስራ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም