ዘርፉ ለብልፅግና ጉዞው ስኬታማነት እያበረከተ ያለውን የላቀ አስተዋጽኦ አጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
ዘርፉ ለብልፅግና ጉዞው ስኬታማነት እያበረከተ ያለውን የላቀ አስተዋጽኦ አጠናክሮ ቀጥሏል
ባሕርዳር፤ ሕዳር 5/2018(ኢዜአ)፡-የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፉ በኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ ስኬታማነት እያበረከተ ያለውን የላቀ አስተዋጽኦ ይበልጥ አጠናክሮ መቀጠሉን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ የ2018 ሩብ የበጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ፤ ዘርፉን በቴክኖሎጂ በማዘመን በሁሉም መስክ ስኬቶችን እያስመዘገበ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በሀገሪቱ በግብርናው፣በማዕድን፣ በቱሪዝም፣ በቴክኖሎጂ ልማትና መሰል እድገት ተኮር ዘርፎች ስኬታማነት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፉ አይተኬ ሚናውን እየተወጣ መሆኑን አንስተዋል።
በዚህም በውሃ፣ በአየርና በየብስ ተደራሽነትን የማሳደግና ዘመናዊነትን የማስፋት ስራ በልዩ ትኩረት እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ዘርፋ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እንዲሳካ አበክሮ በመስራት የሀገር አለኝታነቱን በተግባር አረጋግጧል ብለዋል።
በሀገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነችውን ግዙፏ የጣናነሽ ቁጥር ሁለት ጀልባ ወደ ጣና ሀይቅ በማስገባት አገልግሎት መስጠት ማስቻሉን ጠቅሰው፤ ይህም የውሃ ላይ ትራንስፖርቱን ያዘመነ ነው ብለዋል።
በሀገሪቱ የሚከናወኑ የልማት ስራዎችን በማሳለጥ ተጨባጭ ውጤት የታየበት ዘርፍ መሆኑን ያመለከቱት ሚኒስትሩ፤ ዘርፉ በኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ ስኬታማነት እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፋ ጽሕፈት ቤት ሀላፊ ይርጋ ሲሳይ በበኩላቸው፤ በክልሉ ሰላምን ከማፅናት ባሻገር ታላላቅ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም በባሕር ዳር፣ ጎንደር፣ ደሴ፣ ወልዲያ፣ ኮምቦልቻ፣ ደብረ ብርሃና ሌሎች ከተሞች ሰፋፊ የኮሪደር ልማት ስራ ማከናወን ተችሏል ብለዋል።
ቀጣይም በሌሎች ከተሞች የማስፋት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፋን በቴክኖሎጂ የማዘመን ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
የክልሉን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ በቴክኖሎጂ ታግዞ ተደራሽነትን የማስፋት ስራ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ባለስልጣን ሀላፊ ዘውዱ ማለደ ናቸው።
በመድረኩ የፌዴራልና የክልሎች የዘርፍ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።