በመፍጠንና በመፍጠር ኢትዮጵያን መገንባት የሚያስችል የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም እየተተገበረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በመፍጠንና በመፍጠር ኢትዮጵያን መገንባት የሚያስችል የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም እየተተገበረ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 5/2018(ኢዜአ)፦ በመፍጠንና በመፍጠር ቴክኖሎጂን በመተግበር ኢትዮጵያን መገንባት የሚያስችል የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም እየተተገበረ መሆኑን የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ(ዶ/ር) ገለጹ።
ይህ የተገለጸው የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ባዘጋጀው የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም የተሞክሮ ልውውጥ መድረክ ላይ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) "የመደመር መንግሥት ዕይታ ለዘርፎች እመርታ" በሚል መሪ ሐሳብ በተዘጋጀው ስልጠና ወቅት የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቅ እንዳለበት አቅጣጫ ማስቀመጣቸው ተገልጿል።
የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ(ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ሒደት ኢትዮጵያ ለተሞክሮ ወደ ውጭ መሄድ የለባትም በሚል መነሻ በሀገር ልጆች የተቀረጸ ነው።
በዓለም ላይ የበለጸጉ ሀገራት ጭምር የተሳካ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርምን ለመተግበር እስከ 300 ዓመት ወስዶባቸዋል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በመደመር ዕሳቤ ሪፎርም እንዲደረግ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሠረት የተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከዚህ አንፃር የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሠረት ሥራውን በብቃት እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በሪፎርሙ የመደመር ሥራ ምን እንደሚመስል በተግባር መሬት ላይ አሳይቶናል ብለዋል።
የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙ ቁርጠኝነትና ውጤታማነት የታየበት ድንቅ ስኬት መሆኑን በማንሳት፤ ይህም ከሀገር አልፎ በአፍሪካም ለተሞክሮ መቅረብ እንደሚችል ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በመፍጠርና በመፍጠን ቴክኖሎጂን ተግባራዊ በማድረግ ኢትዮጵያን መገንባት የሚያስችል ሪፎርም ተደርጓል ብለዋል።
ሁሉም የተሳተፉበት በሀገር ልጆች የተሰራ ሪፎርም መሆኑን ጠቅሰው፤ ለሪፎርሙ 14 የትግበራ ስትራቴጂዎች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
ጥሩ የሠሩ ሠራተኞች የሚበረታቱበት ሥርዓት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፤ የሀሳብ ባንክ መዘጋጀቱ ከበለጸጉ ሀገራት ጭምር ቀድመን የሄድንበት ነው ብለዋል።
ሪፎርሙ የሚሠሩ ሥራዎችን ለይቶ ማስቀመጡን ጠቅሰው፣ መተግበሪያ መሣሪያዎች በራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ዕድል መስጠቱን ገልጸዋል።
የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርሙን ለማሳካት የጎላ አበርክቶ ያለው በመሆኑ ለሪፎርሙ ስኬታማነት የተሰጠውን ዕድል በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።