የቀኑ መከበር የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን ለማሳደግ የጎላ አስተዋፅኦ አለው - ኢዜአ አማርኛ
የቀኑ መከበር የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን ለማሳደግ የጎላ አስተዋፅኦ አለው
አዲስ አበባ፤ሕዳር 5/2018 (ኢዜአ)፡-የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር የሕዝቦችን ትሥሥር ለማጎልበት፣የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን ለማሳደግ፣የቱሪዝም መሠረተ ልማቶችን ለማልማት እና ለማስተዋወቅ የጎላ አስተዋፅኦ እንዳለው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
ቀኑ በየዓመቱ መከበሩ፤ የህዝቦች ትስስርን በማጠናከር እና በማጎልበት ህብረ-ብሄራዊ አንድነት በጠንካራ መሰረት ላይ እንዲገነባ ከፍ ያለ ፋይዳ እንዳለውም ጠቁመዋል።
20ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስተናጋጅነት "ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረ ብሄራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ በሆሳዕና ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል ።
ቀኑን ዲሞክራሲያዊ አንድነት እንዲጠናከር እና ኅብረብሔራዊ አንድነት እንዲጎለብት በሚያስችሉ ተግባራት ለማክበር በቂ ዝግጅት መደረጉን ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ርዕሰ መስተዳደሩ በመግለጫቸው የቀኑ መከበር ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች እርስ በእርስ እንዲተዋወቁና ህብረ ብሄራዊ አንድነት እንዲጠናከር ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አንስተዋል።
የልማት ኢኒሸቲቮችን በላቀ ፍጥነትና ጥራት ለማከናወን እድል መፍጠሩን እንዲሁም ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ እና የከተሞች እድገትን እውን በማድረግ የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አስተዋፅኦ አለው ሲሉም ተናግረዋል።
በዓሉ በክልሉ የሚገኙ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ የቱሪስት መዳረሻዎችን፣ ፀጋዎችን እና የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማስተዋወቅ ትልቅ እድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል ።
ከተሞችን የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ በተያዘው አገራዊ አቅጣጫ በመታገዝ በክልሉ በከፍተኛ ህዝባዊ ተሳትፎ የኮሪደር ልማት እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።
ክልሉን የሰላም ተምሳሌት ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት አስተማማኝ ሰላም መፍጠር መቻሉን አስታውቀዋል።
20ኛው የብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ታላቁ የህዳሴ ግድብ ተጠናቆ በተመረቀበት ማግስትና ኢትዮጵያውያን በሀገራዊ አጀንዳዎች በጋራ በቆምንበት ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ የሚከበር በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የቀኑ መከበር የሕዝቦችን ትሥሥር ለማጎልበት፣ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን ለማሳደግ፣ የቱሪዝም መሠረተ ልማቶችን ለማልማት እና ለማስተዋወቅ የጎላ አስተዋፅኦ እንዳለውም ጠቁመዋል።