ቀጥታ፡

ከተሞችን ለኑሮ ምቹ የማድረግ ተግባር በጥናትና ምርምር እየተደገፈ ነው 

ጭሮ ፤ሕዳር 5/2018 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል ከተሞችን ዘመናዊና ለኑሮ ምቹ የማድረግ እንቅስቃሴ በጥናትና ምርምር እየተደገፈ መሆኑን የክልሉ ከተማ ፕላን ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡

ኢንስቲትዩቱ በክልሉ ከተሞች  ላይ ያካሄደውን ችግር ፈቺ የጥናት እና ምርምር ስራዎችን ለባለድርሻ አካላት ያቀረበበት ሲምፖዝየም በጭሮ ከተማ ተካሂዷል፡፡

በዚሁ ወቅት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ መርጋ ኦሊቃ እንዳሉት የክልሉ የከተማ ፕላን ኢንስቲትዩት ከተሞች ዘመናዊ ፕላን እንዲኖራቸው እና በሁሉም ረገድ ያሉባቸውን ችግሮች ለመፍታት በጥናት እና ምርምር የታገዘ ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡


 

ኢንስቲትዩቱ በክልሉ ለሚገኙ አብዛኛዎቹ ከተሞች ዘመናዊና ደረጃውን የጠበቀ ፕላን ማዘጋጀቱን አንስተው በጎርፍ ተጋላጭነት፣ በአካባቢ ልማት እና አረንጓዴ ልማት ላይ ያተኮሩ ሶስት ችግር ፈቺ የጥናት ስራዎች በ14 ከተሞች ላይ መከናወናቸውንም አመልክተዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ ለከተሞቹ ዘመናዊ ፕላን ከማዘጋጀት ባለፈም ለየከተሞቹ አመራርና ባለሙያዎች ድጋፍና ስልጠና በመስጠት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የክልሉን ከተሞች በዘመናዊ መልኩ ለማልማት የተጀመረውን ጥረት በማገዝ ከተሞቹ ሙሉ ለሙሉ ደረጃውን የጠበቀ ፕላን እንዲኖራቸው ትኩረት ተሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በጭሮ ከተማ የተካሄደው ሲምፖዝየምም የጥናትና ምርምሮቹን ግኝት በከተሞቹ ለሚገኙ ባለድርሻ አካላት ለማቅረብ ነው ብለዋል፡፡

በመቱ፣ ገለምሶ፣ አሰላ እና ባቢሌ ከተሞች ላይ በማተኮር በከተሞች መኖሪያ አካባቢ በተካሄደው ጥናት በከተሞቹ የፕላን አዘገጃጀት አሳታፊ ያለመሆን እንደ ዋነኛ ችግር የታየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ በበዴሳ፣ ሳጉሬ፣ ዴራ፣ ቡሌ ሆራ እና ቢሾፍቱ ከተሞች የከተሞች አረንጓዴ ልማት ላይ ያተኮሩ የጥናት ስራዎች ተከናውነው መልካም ጅምሮች እንዳለ ተለይቷል ብለዋል።

የጥናት ስራውን ካከናወኑ  መካከል በኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ መምህር  ንጉሴ ደበሌ (ዶ/ር) እንዳሉት ቀደም ሲል የተገነቡ ግንባታዎች በተገቢው እና ደረጃውን በጠበቀ ፕላን ባለመገንባታቸው ከተሞች ዘመናዊና  ምቹ እንዳይሆኑ አድርጓል፡፡


 

በአሁኑ ወቅት መንግስት ከተሞችን ዘመናዊና ለኑሮ ተስማሚ ለማድረግ የጀመረውን ጥረት የሚያግዝ ችግር ፈቺ የጥናት ስራ  ማከናወናቸውን አመልክተዋል፡፡

መንግስት ከተሞችን በዘመናዊ መልኩ ለማልማት የጀመረው ጥረት የአገሪቱን ብልጽግና የሚያረጋግጥ በመሆኑ ባለድርሻ አካላት ሊደግፉት ይገባል ብለዋል።

የገለምሶ ከተማ ከንቲባ አቶ መሀመድ አብደላ በበኩላቸው በኢንስቲትዩቱ የተከናወነው የጥናት ስራ በርካታ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን የጠቆመና ከተሞችን ለማዘመን እየተደረገ ያለውን ጥረት የሚያግዝ እንደሆነ አንስተዋል፡፡


 

በሲምፖዝየሙ ላይ ከተለያዩ የክልሉ ከተሞች የተውጣጡ ባለሙያዎች እንዲሁም የጭሮ ከተማ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም