ቀጥታ፡

ቅርሶችን በመጠበቅ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸውን ለማጎልበት የተሰሩ ተግባራት አበረታች ውጤቶች እያስገኙ ነው

ድሬዳዋ፤ ህዳር 5/2018(ኢዜአ)፦ ቅርሶችን በመጠበቅ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸውን ለማጎልበት የተሰሩ ተግባራት አበረታች ውጤቶች እያስገኙ መሆኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ህይወት ኃይሉ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን " በተቀናጀ ትብብር ህገ ወጥ የቅርስ ዝውውርን እንከላከል " በሚል መሪ ሃሳብ ህገ- ወጥ የቅርስ ዝውውር መከላከል ዓለምአቀፍ ቀንን ዛሬ በድሬዳዋ በውይይት አክብሯል ።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ህይወት ኃይሉ በወቅቱ እንዳሉት ቅርሶችን በመጠበቅ ለአገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚያበረክቱትን ፋይዳ ለማጎልበት የተሰሩ ተግባራት አበረታች ውጤቶች እያስገኙ ነው።

ቅርሶችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመመዝብ፣ ደረጃ በማውጣትና በማልማት ሁለንተናዊ አብርክቷቸውን እውን ለማድረግ በትኩረት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በፌደራልም ሆነ በክልሎች የሚገኙ ቅርሶች ላይ ምርምሮችና ዕድሳትን በማካሄድ ቅርሶቹ ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉም እየተሰራ መሆኑን አክለዋል።

በተለይ ከለውጡ በኃላ ለቅርሶች ጥበቃና እድሳት ልዩ ትኩረት በመስጠት ለቱሪስት መዳረሻ እንዲያገለግሉ መደረጉን አንስተዋል።

በጅማ አባጅፋር፣ በጎንደር፣ በሶፍ ኡመር ዋሻ እና በሌሎች ቅርሶች ላይ የተሰሩ ስራዎችንም በማሳያነት አቅርበዋል።

ከእድሳትና ጥበቃ በሻገርም በተለያዩ ወቅቶች በህገ ወጥ መንገድ ከአገር የወጡ 44 ቅርሶችን ከቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ ጋር በመቀናጀት ማስመለስ መቻሉን ተናግረዋል ።

እነዚህን አበረታች ስራዎች ለማጠናከርና ህገ ወጥ የቅርስ ዝውውርን ለመከላከል ከአየር መንገድ፣ ከጉምሩክ፣ ከፍትህና ፀጥታ ፣ ከኃይማኖት አባቶች ጋር ዛሬ የተካሄደው ውይይት አጋዥ እንደሚሆን ጠቁመዋል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የድሬዳዋ አስተዳደር የባህልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንደሰን አባይ በበኩላቸው ከባለስልጣኑ ጋር በመቀናጀት ቅርሶችን የመጠበቅ፣ የማልማት፣ የማደስና የመመዝገብ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።

በተለይ ባለስልጣኑ፣ የ16ተኛዉ ክፍለ ዘመን የስልጣኔ አምባ የነበረውን የሐርላ መካነ ቅርስ እና 130 አመታት ያስቆጠረው የባቡር ተርሚናል በተገቢው መንገድ በማደስ ለቱሪስት መዳረሻነት እንዲውሉ መደረጉ ከዘርፉ የተሻለ ጥቅም እንዲገኝ መደላድል መፈጠሩን ጠቅሰዋል።

እነዚህን ሃብቶች በተገቢው መንገድ መጠበቅና መንከባከብ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል ።

የተካሄደው የግንዛቤ ማጎልበቻ ውይይት በዘርፉ የተጀመሩ አበረታች ስራዎችን ተቀናጅቶ ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም