ቀጥታ፡

የስንዴ ምርትን ከብክነትን በፀዳ መልኩ የመሰብሰብ ተግባር በምስራቅ ጉራጌ ዞን

ወልቂጤ፤ ህዳር 5/2018 (ኢዜአ)፦ የደረሰ የስንዴ ሰብል ምርትን በኮምባይነር በመታገዝ ብክነትን በሚቀንስ መልኩ እየሰበሰቡ መሆኑን የምስራቅ ጉራጌ ዞን አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡

መንግስት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በግብርናው መስክ ከጀመራቸው ተግባራት መካከል የስንዴ ልማት በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው፡፡

ይህም ከውጪ ይገባ የነበረውን የስንዴ ምርት በሀገር ውስጥ በመተካት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጪን አስቀርቷል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ስንዴን በሰፋፊ ማሳዎችና በቴክኖሎጂ በመታገዝ የማልማት ስራው የተጠናከረ ሲሆን በተለያዩ አካባቢዎችም በኩታ ገጠም አስተራረስ አርሶ አደሮችን በማደራጀት እየተከናወነ ነው፡፡

በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምስራቅ ጉራጌ ዞንም የስንዴ ልማት ስራው በትኩረት እየተከናወነ ሲሆን የደረሰውም ምርት በኮምባይነር በመታገዝ ፈጥኖ በመሰብሰብ የምርት ብክነትን ለመከላከል እየተሰራ ነው፡፡

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የዞኑ አርሶ አደሮች እንደተናገሩትም የደረሰ የስንዴ ምርታቸውን በኮምባይነር በመታገዝ ከብክነት በጸዳ መልኩ እየሰበሰቡ ነው፡፡

በምስራቅ መስቃን ወረዳ የባቲሊጃኖ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር መለሰ ኡርጋቶ በመኸር ወቅት ከ4 ሄክታር በላይ መሬትን በስንዴ ሰብል ማልማታቸውን ገልጸዋል፡፡

በባለሙያዎች ክትትልና ድጋፍ በመታገዝ ያለሙትን የስንዴ ሰብል ከብክነት በጸዳ መልኩ በኮምባይነር መሰብሰባቸውን ተናግረዋል።

በሶዶ ወረዳ የኤጀርሳ ቀበሌ አርሶ አደር ሃይሌ ሀብታሙ በበኩላቸው በመኸር ወቅት ሦስት ሄክታር የሚጠጋ ማሳን በስንዴ ሰብል ማልማታቸውን ጠቁመዋል፡፡

የደረሰውን የስንዴና የጤፍ ሰብላቸውን ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ ለመከላከል ቀድመው እየሰበሰቡ እንደሚገኙ ገልጸው፤ ጊዜና ጉልበት የሚቆጥቡና ምርትን ያለ ብክነት ለመሰብሰብ የሚያስችሉ ዘመናዊ ማሽኖች በመንግስት እንደተመቻቸላቸውም ተናግረዋል፡፡

የምስራቅ ጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ደሱ አበጋዝ እንዳሉት በዞኑ ለምግብ ፍጆታና ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውል ስንዴ በስፋት እየተመረተ ነው፡፡

በዞኑ በመኸር ከተሸፈነው ከ20 ሺህ ሄክታር በላይ የስንዴ ማሳ 13 ሺህ 772 ሄክታሩ በኩታ ገጠም የለማ መሆኑን ጠቅሰው ከ1 ሚሊዮን 300 ሺህ በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡

የደረሱ ሰብሎችን በፍጥነትና ከብክነት በጸዳ መልኩ በማሽን በመታገዝ የመሰብሰብ ተግባር እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡

ስንዴን ጨምሮ የደረሱ ሰብሎችን ፈጥነው በመሰብሰብ ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብና የምርት ብክነት የመከላከል ተግባር እየተከናወነ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የሶዶ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና ግብርና ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሸጋ ሃብቴ ናቸው።

የምስራቅ መስቃን ወረዳ ግብርና ፅህፈት ቤት ምክትልና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሁሴን ሙስጠፋ በበኩላቸው በወረዳው ምርትን ከብክነትን በፀዳ መልኩ በመሰብሰብ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም