ሳይንስና ቴክኖሎጂ
ስታርት አፖች ለኢትዮጵያ እድገት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ የሚደረጉ ድጋፎች ሊጠናከሩ ይገባል
Apr 13, 2024 362
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 5/2016(ኢዜአ)፦ ስታርት አፖችን ለማጠናከርና ለኢትዮጵያ እድገት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ የሚደረጉ ድጋፎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ቀረበ። ከመጋቢት 30 እስከ ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆየው የኢትዮጵያ "ስታርት አፕ" አውደ-ርዕይ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በሳይንስ ሙዚየም ለጎብኚዎች ክፍት ተደርጓል። በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በኢንዱስትሪ፣ በፋይናንስና በሌሎች ዘርፍ የተሰማሩ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ''ስታርት አፖች'' በአውደ-ርዕዩ በመሳተፍ ላይ ናቸው።   አውደ-ርዕዩ የተዘጋጀው በአገሪቱ የሚገኙ ስታርት አፖች ያላቸውን ምርትና አገልግሎት እንዲሁም ፈጠራዎች ተደራሽ ማድረግ ነው። ኢዜአ ያነጋገራቸው በአውደ-ርዕዩ የተሳተፉ፤ ስታርት አፖች ለኢትዮጵያ እድገትና ብልጽግና የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ለዘርፉ የሚደረጉ ዘርፈ-ብዙ ድጋፎች መጠናከር እንዳለባቸው ይናገራሉ። ቴክኖሎጂ አልሚዎችን ከገበያው ጋር ለማገናኘት የሚሰራው የኢቴክ ቴክኖሎጂ የማርኬቲንግና የሪሌሽንሺፕ ቺፍ ኦፊሰር እስጢፋኖስ ብርሃኑ፤ ድርጅታቸው አጠቃላይ የቴክኖሎጂ አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሷል። በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አምና በተዘጋጀ ውድድር ከ90 ስታርት አፖች ተመርጠው ወደ ሞሮኮ ከተጓዙት መካከል መሆናቸውን ጠቅሶ፤ ቴክኖሎጂን በአውትሶርሲንግ (በሦስተኛ ወገን) የሚያሰራ አይ ቲኦ የሚባል ቴክኖሎጂ ማቅረባቸውን ያነሳል። አሁን ላይ ለስታርት አፕ የተሰጠው ትኩረት በዘርፉ የተሰማሩ ወጣቶች አቅማቸውን ለማጎልበትና ለአገሪቱ እድገት አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ የሚያግዝ መሆኑን ገልፆ፤ ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግሯል። የማሜ መጫወቻዎችና ፐዝሎች መሥራች ዘሩባቤል መስፍን በበኩሉ፤ በቴክኖሎጂው የቀረቡት ፊደል እያንዳንዱ ፊደል በድምፅ የሚያስተምር፣ ቁጥሮችንና አባታዊ ምክሮች ብሎም ሙዚቃዎችና ግጥሞች ያካተተ ነው። በሳይንስ ሙዚየም እየተካሄደ ያለው አውደ-ርዕይ ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅና ከደንበኞች ጋር ለመገናኘት እንደሚጠቅም ገልፆ፤ ከሌሎች መሰል ስታርት አፖች ጋር የልምድ ልውውጥ ለማድረግም ያግዛል ብሏል። የሚሰራበትን ቴክኖሎጂውን ለማበልፀግ አንዳንድ ግብዓቶች ከውጭ የሚመጡ መሆኑን ገልፆ፤ ቀደም ሲል በግብዓቶች ላይ የሚጣለው ቀረጥ ከፍተኛ እንደነበርና አሁን ላይ የዋጋ ቅናሽ መደረጉ የሚበረታታ ነው ብሏል። በዚህ ረገድ ያሉት የማሻሻያ ሥራዎች ይበልጥ ሊጠናከሩ ይገባል ነው ያለው።   አሁን ላይ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን የሚሰራው ኢኔብለር ቴክ መሥራችና ሥራ አስፈጻሚ ይድነቃቸው ከድር በበኩሉ፤ መንግሥት የስታርት አፖች ምህዳሩን ምቹ ለማድረግ የሚሰራቸው ሥራዎች የሚበረታታና ሊጠናከር የሚገባው ነው ብሏል። ስታርት አፖች ሥራቸውን ይዘው የሚያቀርቡባቸው ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ መድረኮች የበለጠ አዳዲስ ኃሳብ እንዲያፈልቁ የሚያግዙ እንደሆኑም ተናግረዋል። ስታርት አፖች ለተለያዩ አገራት እድገት አስተዋጽዖ ማድረጋቸውን ጠቅሰው፤ በኢትዮጵያም ሚናቸውን እንዲወጡ የባለኃብቶች ድጋፍ ወሳኝ መሆኑንም ገልፀዋል።  
ብሔራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት የመጀመሪያ ስብሰባውን አካሄደ
Apr 12, 2024 620
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 4/2016(ኢዜአ):- ብሔራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት የመጀመሪያ ስብሰባውን አካሂዷል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር በለጠ ሞላ በዚሁ ወቅት፤ ምክር ቤቱ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ እና ስራዎቹን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በየጊዜው ሪፖርት እንደሚያደርግ አብራርተዋል፡፡ የምክር ቤቱ በ1205/2012 የፀደቀው የኤሌክትሮኒክስ ግብይት አዋጅ መሰረት አድርጎ የተቋቋመ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሚመለከታቸው ተቋማት እና ባለድርሻ አካላት የምክር ቤቱ አባላት እንደሆኑም ተናግረዋል።   ምክር ቤቱ ቅንጅታዊ አስራርን በመዘርጋት አስፈላጊ የሆኑ ስራዎችን በመለየት የፖሊሲ እና የስትራቴጂ ምክረ ሃሳብ በማቅረብ እና የወጡ ፖሊሲዎች ውጤታማነት የሚገመግም መሆኑንም እንዲሁ፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ የወጡ የዲጂታል እና ቴክኖሎጂ ፓሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች ተፈፃሚነታቸውን በየጊዜው መከታተል አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ምክር ቤቱ ይህንን ታሳቢ በማድረግ መደራጀቱን ጠቁመዋል፡፡ ይህም የኢትዮጵያን ዲጂታል ጉዞ ውጤታማ በማድረግ ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የወጡ ፖሊሲዎች በውጤታማነት እንዲተገበሩ የመከታተል ተግባራትንም እንደሚያከናውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡   የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ በበኩላቸው ምክር ቤቱ ቅንጅታዊ አስራርን በማጎልበት በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዘርፍ ኢትዮጵያ ያቀደቻቸውን ዕቅዶች እንድታሳካ የሚያስችል ነው ብለዋል።   ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 እውን ለማድረግ የተጀመሩ ተግባራትን የበለጠ የሚያጠናክርበት ዙሪያ ላይ እንደሚሰራ የተናገሩት ደግሞ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ናቸው፡፡ ምክር ቤቱ በዛሬ ስብሰባው ቀደም ብሎ ተቋቁሞ በነበረው ግብረ ሃይል የተሰሩ ስራዎችን ሂደት የተመለከተ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይ በሚሰሩ ስራዎች ዙሪያ አቅጣጫ ማስቀመጡንም ጠቁመዋል፡፡ እስካሁን ባለው ሂደትም ከ132 ተቋማት መካከል 108 የሚሆኑት ወደ ዲጂታል ዳታ ማዕከል መረጃቸውን ማስገባታቸውን ተናግረዋል፡፡
የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ውጤቶችን በመደገፍ  በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የላቀ ውጤት እንዲመዘገብ እየተሰራ ነው -ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Apr 12, 2024 530
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 4/2016(ኢዜአ)፦ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ውጤቶችን በመደገፍ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የላቀ ውጤት እንዲመዘገብ እየተሰራ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ። "ደስታ" የተሰኘችው ሮቦት ከአንጋፋው የጃዝ ሙዚቃ ባለሙያ ሙላቱ አስታጥቄ ጋር በመሆን የሙዚቃ ትእይንት ትላንት ምሽት በአዲስ አበባ አቅርባለች። በመርኃ-ግብሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣የሥራ ፈጠራና ቴክኖሎጂ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስና ቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ትኩረት ስጥታ እየሰራች ነው፡፡   አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የዓለም የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይ በኢትዮጵያም ሆነ በአህጉሪቷ የሚስተዋሉ ውስብስብ ችግሮችን ለመፍታት ሁነኛ መፍትሄ እንደሚሆንም ነው የገለጹት፡፡ በመሆኑም መንግስት የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት በማቋቋም ጭምር አርቴፊሻል ኢንተሌጀንስና ሌሎች የዲጂታል አማራጮችን ለማጠናከር በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ እንደ "ደስታ" ያሉ የሰው ሰራሽ አስተውሎቶችን በመፍጠር ለዲጂታል ትራስፎርሜሽን ግንባታ የሚሰጠው ትኩረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።   የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተሌጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና በበኩላቸው፣የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እንደ ሀገር የተጀመረውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን በማገዝ በዘርፈ ብዙ መስኮች ላይ ለመጠቀም የሚያስችል ነው ብለዋል። በዚህም ፣በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣በኢንዳስትሪ ፓርኮችና ሌሎችም ዘርፎች የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በመጠቀም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ እንድትሆን እየተሰራ ነው ብለዋል። "ደስታ" ሮቦት የሙዚቃ ትዕይንት መርኃ ግብር እንድታሰናዳ የተደረገው የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስና አይኮግ ላብስ ከኢትዮጵያ አየር መንገድና ኢትዮ-ቴሌኮም ጋር በመተባበር ነው። ደስታ ሮቦት የአማርኛ ቋንቋን ለመናገር የሚያስችል ፕሮግራም የተጫነላት ሲሆን በመርኃ ግብሩ በአማርኛ ንግግር አሰምታለች። የኢትዮ-ቴሌኮም 5ኛ ትውልድ ቴክኖሎጂን በመጠቀምና በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በቋንቋ ቅንብር አማርኛ ቋንቋ የምትናገረው ''ደስታ'' በአይኮግ ላብስ እንደለማች ነው የተገለጸው፡፡ ደስታ የአማርኛ ቋንቋን የምትናገር፣ የግርምት፣ ደስታና ሌሎች ስሜቶችን የምታንጸባርቅ ብሎም መደነስ የምትችል ሮቦት ናት።  
በኢትዮጵያ ስታርት አፖችን በስፋት ወደ ገበያው ለማስገባት ሥነ ምህዳሩን ምቹ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ ነው
Apr 12, 2024 234
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 4/2016(ኢዜአ):- በኢትዮጵያ ስታርት አፖችን በፍጥነት፣ በጥራትና በስፋት ወደ ገበያው ለማስገባት ሥነ ምህዳሩን ምቹ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ። ከመጋቢት 30 እስከ ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆይ የኢትዮጵያ "ስታርት አፕ" አውደ ርዕይ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በሳይንስ ሙዚየም ለጎብኚዎች ክፍት ተደርጓል። በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በኢንዱስትሪ፣ በፋይናንስና በሌሎች ዘርፍ የተሰማሩ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ''ስታርት አፖች'' በአውደ ርእዩ በመሳተፍ ላይ ናቸው። አውደ ርዕዩ ስታርት አፖች ያላቸው ምርት፣ አገልግሎትና ፈጠራዎች ተቋማት፣ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎችና ተማሪዎች እንዲጎበኙ ማድረግ ያለመ ነው። በባለኃብቶችና በስታርት አፖች መካከል ትስስር እንዲፈጠር ማድረግ ሌላው የአውደ ርዕዩ ዓላማ ሲሆን ስታርት አፖች ያላቸውን ጥንካሬ ማስቀጠል፤ ክፍተት የሚታይባቸውን ቦታ ለይቶ ድጋፍ የሚያገኙበት ሁኔታ ማመቻቸትም እንዲሁ። በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ደኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ስታርት አፖችን በፍጥነት፣ በጥራትና በስፋት ወደ ገበያው እንዲገቡ ሥነ ምህዳሩን ምቹ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ ነው። በትምህርት ፖለሲ ደረጃ ለሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግና ሂሳብ ትምህርቶች ትኩረት መሰጠቱ በዲጂታል ኢኮኖሚ ዕዳን ወደ ምንዳ ለመለወጥ ትልቅ ዕድል የሚሰጥ መሆኑን አብራርተዋል። በዲጂታል ዘርፉ ኦንላይን አገልግሎቶች በስፋት ተግባራዊ መደረጉ በመስኩ ወደ ገበያው የሚገቡ ስታርት አፖች ቁጥር ከፍ የማድረግ አወንታዊ ሚና እንዳለውም ጠቅሰዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በሰጡት አቅጣጫ ስታርት አፖች ያሉ መልካም ዕድሎችን ተጠቅመው ውጤታማ እንዲሆኑ የመደገፍ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል። ለዚህም የፖለሲና ማበረታቻ ድጋፎች አሰራር በመዘርጋቱ የአጭር፣የመካከለኛና የረጅም ጊዜ የድጋፍ ማዕቀፎች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ስታርት አፖችን ለመደገፍና ለማበረታታት የተዘረጋው አሰራር የውጭ ስታርት አፖችን የሚጋብዝ ስለመሆኑም አንስተዋል። በስታርት አፕ ኢትዮጵያ አውድ ርዕይ በርካታ አዳዲስ አገልግሎቶች፣ ፈጠራዎችና ፕሮጀክቶች መቅረባቸውን ጠቅሰው ተጨባጭ ውጤት እንዲያመጣም ድጋፍ ይደረጋል ሲሉ አረጋግጠዋል። ለዚህም ከመስሪያ ቦታ አቅርቦት፣ የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፎችን የሚያገኙበት ሁኔታዎች ማመቻቸት ላይ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል። በኢትዮጵያ ስታርት አፖችን ደግፎ ወደ ገበያ እንዲገቡ ማድረግ በተለይም ለወጣቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል። በግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝምና ሌሎችም መስኮች ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድም የስታርት አፖች አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑን ጠቅሰዋል። በኢትዮጵያ አሁን ላይ ከ900 በላይ ስታርት አፖች መኖራቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።  
ኢትዮጵያ ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የሰጠችው ትኩረት ተጠናክሮ ይቀጥላል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Apr 11, 2024 416
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 3/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለአርቴፊሻል ኢንተለጀንስና ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የሰጠችው ትኩረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለፁ። ደስታ የተሰኘችው ሮቦት በስካይ ላይት ሆቴል ከአንጋፋው የጃዝ ሙዚቃ ባለሙያ ሙላቱ አስታጥቄ ጋር በመሆን ሙዚቃዋን ዛሬ ምሽት ታቀርባለች። በመርኃ-ግብሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሥራ ፈጠራና ቴክኖሎጂ ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። አቶ ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በአርቴፊሻል ኢንትለጀንስና በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ በትኩረት እየሰራች ነው። አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የኢትዮጵያንም ሆነ የአህጉሪቱን ችግሮች ለመፍታት ሁነኛ መፍትሄ እንዲሁም የወደፊት የዓለም የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አንስተዋል። ይህንንም ተከትሎ እንደ ደስታ ሮቦት ያሉ የሰው ሰራሽ አስተውሎቶችን በመፍጠር ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ግንባታ የሚሰጠው ትኩረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።   ደስታ ሮቦት የዛሬውን የሙዚቃ መርኃ ግብር እንድታሰናዳ የተደረገው የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስና አይኮግ ላብስ ከኢትዮጵያ አየር መንገድና ኢትዮ-ቴሌኮም ጋር በመተባበር ነው። ደስታ ሮቦት የአማርኛ ቋንቋን መናገር የሚያስችል ፕሮግራም የተጫነላት ሲሆን በመርኃ ግብሩ በአማርኛ ንግግር አሰምታለች። የኢትዮ-ቴሌኮም 5ኛ ትውልድ ቴክኖሎጂን በመጠቀምና በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በቋንቋ ቅንብር አማርኛ ቋንቋ የምትናገረው ደስታ ሮቦት በአይኮግ ላብስ ነው የለማችው። ደስታ የአማርኛ ቋንቋን የምትናገር፣ የግርምት፣ ደስታና ሌሎች ስሜቶችን የምታንጸባርቅ ብሎም መደነስ የምትችል ሮቦት ናት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የስታርት አፕ ኢትዮጵያ አውደ ርዕይን ጎበኙ
Apr 11, 2024 215
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 3/2016(ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሳይንስ ሙዚየም በተከፈተው የ'ስታርት አፕ' ኢትዮጵያ አውደ ርዕይ እየተሳተፉ የሚገኙ ስታርት አፖችን ጎበኙ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት በሳይንስ ሙዚየም እየታየ ያለው የ'ስታርት አፕ' ኢትዮጵያ አውደ ርዕይ በዘርፉ ያሉ ተሳታፊዎችን ተምኔት፣ የፈጠራ ምናብ ስፋት ብሎም ችሎታ ማሳያዎች የቀረቡበት ነው ብለዋል። በመሆኑም ሁላችሁም አውደ ርዕዩን በመመልከት ከተሳታፊዎቹ ጋር እንድትወያዩ እጋብዛለሁ ሲሉም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ያቀረቡት። በአውደ ርዕዩ እየተሳተፉ የሚገኙ ስታርት አፖች፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ስራዎቻቸውን በመመልከት እንዳበረታቷቸው ተናግረዋል። የፕላስቲክ ቆሻሻን ወደ ተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ምርቶች በመቀየር ላይ የተሰማራው የኩቢክ ስታርት አፕ ተወካይ ኤዶም ዳዊት፥ ኩቢክ የፕላስቲክ ቆሻሻን በመሰብሰብ በአነስተኛ ወጪ የሚገነቡ ቤቶችን ለመስራት የሚያገለግሉ ቁሶችን ወደ ማምረት መሸጋገሩን ገልጻለች።   ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በአውደ ርዕዩ ተገኝተው ስራዎቻቸውን እንደተመለከቱ የጠቀሰችው ወጣት ኤዶም፥ መንግስት ስታርት አፖችን ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት እንዳረጋገጡም ተናግራለች። በኤሌክትሪክ ለሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ሃይል የማቅረብ ዓላማ ይዞ የተነሳው ኢትዮ ቻርጅ የተሰኘው ስታርት አፕ ተወካይ ወጣት አብዱ ጀማል፥ የሃይል መሙያ መሰረተ ልማቶችን በሙከራ ደረጃ መትከል መጀመራቸውን ጠቁሟል።   ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በኤግዚቢሽኑ ተገኝተው እንዳበረታቷቸው የጠቀሰው ወጣት አብዱ፥ መንግስት ለስታርት አፖች የፖሊሲ እርምጃዎችን በመውሰድ፣ ኤግዚቢሽኖችን በማዘጋጀት ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ገልጿል። የኢኔብለር ቴክ ተባባሪ መስራች እና ዋና ስራ አስፈጻሚ ይድነቃቸው ከድር፥ የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ስርዓት የሚያዘምን በተገልጋይ ቤተሰብና በአገልግሎት ሰጪው መካከል እንግልትን የሚቀርፍ ስርዓት ይዘው መምጣታቸውን አስረድቷል።   በሳይንስ ሙዚየም የተከፈተው አውደ ርዕይ ስታርት አፖች እርስ በርስ እንዲተዋወቁና ልምድ እንዲካፈሉ፣ ከድርጅቶች ጋር ትስስር እንዲፈጥሩ ምቹ ምህዳር እንደሆነላቸውም አንስቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና መንግስታቸው ፈታኝ የሆነውን የስታርት አፕ ምቹ ምህዳርን የመፍጠር ሂደት በቁርጠኝነት መጀመራቸው ለስታርት አፖች ትልቅ ምዕራፍ መክፈቱንም ገልጿል። ስታርት አፖቹ በቀጣይ ወደ ሙሉ ምርት እና አገልግሎት በመግባት ራሳቸውንና ሀገራቸውን ለመለወጥ በትጋት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል። ለአብነትም ኢትዮ ቻርጅ የስራ አድማሱን በማስፋት በቀጣይ በሆቴሎች፣ በነዳጅ ማደያዎችና ሌሎች አመቺ ስፍራዎች መሰረተ ልማቱን ለመትከል እቅድ የያዘ ሲሆን አገልገሎቱን ከሰሃራ በታች ሀገራት እንደሚያስፋፋ ገልጿል። ኢኔብለር ቴክ ደግሞ የአገልግሎት መስመሮችና እና የኃይል ቆጣሪዎችን ክላውድ ቤዝድ ስርዓትን በመጠቀም ለማዘመንና በአገልግሎት ሰጪና በተጠቃሚ ቤተሰብ መካከል ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር እየሰራ ነው ብሏል። ኩቢክ ስታርት አፕ በበኩሉ በኢትዮጵያ ደረጃ የጀመረውን ቆሻሻን የማስወገድ፣ የአካባቢ ጥብቃን የማጎልበት እንዲሁም ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ የማዋል ስራውን አህጉራዊ የማድረግ ህልሙን በአጭር ጊዜ እንደሚያሳካው ነው የጠቆመው። መንግስት ለስታርት አፕ ምቹ ምህዳርን ለመፍጠር የፖሊሲ እርምጃዎችን ይፋ አድርጎ ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል። የስታርት አፕ ኢትዮጵያ አውደ ርዕይ ከመጋቢት 30 እስከ ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በኢንዱስትሪ፣ በፋይናንስና በሌሎች ዘርፍ የተሰማሩ ስታርት አፖች እየተሳተፉበት ነው።
የኢትዮጵያ የግብርና ምርት በዓለም ገበያ ያለውን ተወዳዳሪነት የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎችን የፈጠሩ ስታርት አፖች
Apr 11, 2024 479
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 3/2016(ኢዜአ)፦በስታርት አፕ ኢትዮጵያ አውደ ርዕይ የግብርና ምርትን እሴት በመጨመር በዓለም ገበያ ያለውን ተወዳዳሪነት የሚጨምሩ የፈጠራ ስራዎች ለዕይታ ቀርበዋል። የወጣቶችን የስራ ፈጠራ ለማስተዋወቅ መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም በተከፈተው በዚህ አውደ ርዕይ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በኢንዱስትሪ፣ በፋይናንስና በሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ''ስታርት አፖች'' እየተሳተፉ ነው። ከነዚህም መካከል ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልካቸውን የግብርና ምርቶች እሴት በመጨመርና የተደራጀ መረጃ ለገዥዎች በማቅረብ ገቢን ለመጨመር የሚያግዙ የፈጠራ ስራዎችን ያቀረቡ ወጣቶች ይገኙበታል። ወጣት ሚኪያስ እስጢፋኖስ በኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው የቡና ምርት መረጃን ገዥው መከታተል የሚችልበት "ትሬሲንግ ኮፊ" የተሰኘ ቴክኖሎጂን አቅርቧል። ይህ ቴክኖሎጂ ከአምራቹ ጀምሮ የቡናን አጠቃላይ መረጃ ገዥው እንዲያውቅ የሚያደርግ ነው ብሏል። በዚህም የኢትዮጵያ ቡና ልዩነቱና ጥራቱ የተረጋገጠ ስለመሆኑ ግልፅ መረጃ ለገዥዎች በመስጠት በዓለም ገበያ ያለውን ተወዳዳሪነት የበለጠ ማሳደግ የሚያስችል መሆኑን አብራርቷል። የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያና የእርሻ ማሽኖችን የሚያመርተው የ"ግሪን ቢን ማኑፋክቸሪንግ" ስራ አስኪያጅ አንዱዓምላክ መሃሪው፥ የወጪ ንግድ ምርቶችን እሴት ለመጨመር ጥቅም ላይ የሚውሉ የፈጠራ ስራዎችን አቅርቧል።   ቴክኖሎጂው የግብርና ምርትን እሴት ጨምሮ በመላክ ገቢንና ተወዳዳሪነትን ለመጨመር የሚያግዝ መሆኑን አብራርቷል። የአዝመሪኖ፣ እርድና ቡና ማድረቂያና መቁያ ማሽኖች ከፈጠራ ስራዎቹ መካከል እንደሚገኙበትም ጠቅሷል። የ"ቢፋርም ቴክ" መስራችና ስራ አስኪያጅ በጋሻው መብራቴ በተመረቀበት የግብርና ሙያ በተለያዩ ተቋማት ተቀጥሮ ሲሰራ ያስተዋለው የግብርና ቴክኖሎጂ እጥረት ለፈጠራ ስራው መነሻ እንደሆነው ተናግሯል። አርሶ አደሩን ከእህል መውቂያ ትራክተር ባለቤቶች እንዲሁም የትራክተር ኦፕሬተር ሙያተኞች ጋር የሚያገናኝ ቴክኖሎጂ እንደፈጠረ አብራርቷል።   ይህም የግብርና ስራን ለማዘመን በሚደረገው ጥረት የራሱን አስተዋጽኦ ለማድረግ እንደሚያግዘው በመጠቆም፥ መንግስት ለፈጠራ ስራ የሰጠው ትኩረት ውጤታማ ለመሆን ተስፋ እንደሰጠው አንስቷል። የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎቹ እንደገለጹት፥ በአውደ ርዕዩ መሳተፋቸው ከባለሃብቶች፣ ፋይናንስ ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የመገናኘት እድልን ፈጥሮላቸዋል። የኢትዮጵያ "ስታርት አፕ" አውደ ርዕይ እስከ ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን የመጀመሪያ ደረጃ፣ የመጀመሪያ ደረጃን የተሻገሩና ወደ ገበያ የመቀላቀል ደረጃ ላይ የደረሱ ስታርት አፖች ስራዎቻቸውን አቅርበዋል። በኢትዮጵያ ሃሳብ ያላቸው ወጣቶች ለዲጂታል ምጣኔ ሃብት ግንባታ፣ ለስራ ፈጠራ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እንዲያውሉ መንግስት በፖሊሲ ደረጃ ልዩ ትኩረት ሰጥቷል።    
መንግስት ለሰውሰራሽ አስተውሎት ተገቢውን የፋይናንስና የፖሊሲ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል - ገንዘብ ሚኒስቴር
Apr 10, 2024 468
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 2/2016(ኢዜአ)፦ መንግስት ለሰውሰራሽ አስተውሎት ተገቢውን የፋይናንስና የፖሊሲ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ። የኢትዮ-ቴሌኮም 5ጂ ቴክኖሎጂን በመጠቀምና በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በቋንቋ ቅንብር አማርኛ ቋንቋ የምትናገር ''ደስታ'' ሮቦት በአይኮግ ላብስ ለምታ በሳይንስ ሙዚየም ለእይታ ቀርባለች።   የደስታ ሮቦትን ጨምሮ በስታርት አፕ ኤግዚቢሽን የቀረቡ ስራዎችን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እየጎበኟቸው ነው። በዚህ ወቅት የገንዘብ ሚኒስቴር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እንዳሉት በዓለም ላይ አዲስ የሆነውን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ ለመጠቀም መንግስት የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ተቋም አቋቁሞ እየሰራ ይገኛል። ኢንስቲትዩቱም በጤና፣ ግብርናና በሌሎች የተለያዩ ዘርፎች ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም ተጨማሪ አቅም እየፈጠረ እንደሆነም ተናግረዋል። የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ትኩረት ከሰጣቸው ከአምስቱ የልማት ምሰሶዎች አንዱ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው የሰው ሰራሽ አስተውሎትም በዚህ ስር የሚመደብ መሆኑን ገልፀዋል። መንግስት ለሰው ሰራሽ አስተውሎት ተገቢውን የፋይናንስና የፖሊሲ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል። የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ተስፋዬ ዘውዴ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ችግሮችን ለመፍታት እንዲያስችሉ ከሚሰራቸው ቴክኖሎጂዎች መካከል ሮቦቲክ ቴክኖሎጂ አንዱ ነው።   በኢንስቲትዩቱ በተለያዩ የአገርኛ ቋንቋዎች መናገር የሚችሉ ሮቦቶች ተሰርተው ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆኑን አንስተዋል። ከዚህ ቀደም የማሽን ቋንቋ ስላልነበር የአገር ውስጥ ቋንቋዎች ሳይንሳዊ ምርምሮችን ለማድረግና ችግሮችን ለመፍታት እገዛ ሳያደርጉ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል። አሁን ላይ ኢንስቲትዩቱ በተፈጥሮ ቋንቋ ቅንብር አራት የአገር ውስጥ ቋንቋዎችን ወደ ማሽን ማስገባት ችሏል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ። ደስታ ሮቦትም በቋንቋ ቅንብር አማርኛን ተጠቅማ ታዳጊዎችና ህፃናት ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ለማነሳሳት ታስባ መቅረቧን ተናግረዋል። የአይኮግላብ ዋና አማካሪ ቤተልሄም ደሴ በበኩላቸው የደስታ ሮቦት ለእይታ መቅረቧ ህፃናትና ወጣቶች መሰል ስራዎችን እንዲሰሩ ለማበረታታት የሚያስችል እንደሆነ ተናግረዋል።   የደስታ ሮቦትን ጨምሮ የተለያዩ የስታርትአፕ አውደ ርዕይ በቀረበበት በሳይንስ ሙዚየም ሲጎበኙ ያገኘናቸው አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው ኤግዚቢሽኑ ህፃናትና ታዳጊዎች ኢትዮጵያ በሳይንስ ዘርፍ የደረሰችበትን እንዲረዱ የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።   ደስታ ሮቦት በዛሬው እለት በሳይንስ ሙዚየም ከምታደርገው ቆይታ ባለፈ በነገው እለት ከአርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ ጋር የጃዝ ምሽት እንደሚኖራት ተገልጿል። በመጪው አርብ ደግሞ በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ከሌሎች በኢንስቲትዩቱ ከተሰሩ ሮቦቶች ጋር ለዕይታ እንደምትቀርብ ተጠቁሟል።  
ደስታ የተሰኘች ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም ለእይታ ቀረበች
Apr 10, 2024 324
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 2/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እና አይኮግ ላብስ ከሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር ደስታ የተሰኘች ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም ለእይታ አቀረቡ። ህፃናት፣ ወጣቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በሳይንስ ሙዚየም በመገኘት የደስታ ሮቦትን ጨምሮ በስታርት አፕ ኤግዚቢሽን የቀረቡ ስራዎችን እየጎበኙ ነው። በዚህ ወቅት የገንዘብ ሚኒስቴር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እንዳሉት ኢትዮጵያ ዓለም የደረሰበት አዲሱ የቴክኖሎጂ እውቀት የሆነው ሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ በትኩረት እየሰራች ነው።   ደስታ ሮቦትም በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት አማርኛ እንድትናገር ተደርጋ መቅረቧን አንስተው፥ ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዓለም የደረሰበት ደረጃ ለመድረስ እየሰራች መሆኑን ጠቅሰዋል። ደስታ ሮቦት በዛሬው እለት በሳይንስ ሙዚየም ከምታደርገው ቆይታ ባለፈ በነገው እለት ከአርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ ጋር የጃዝ ምሽት እንደሚኖራት ተገልጿል። በመጪው አርብ ደግሞ በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ከሌሎች በኢንስቲትዩቱ ከተሰሩ ሮቦቶች ጋር ለዕይታ እንደምትቀርብ ተጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ስታርት አፕ አውደ ርዕይ አገሪቱ  በዘርፉ ያላትን እምቅ አቅም ያመላከተ ነው
Apr 10, 2024 388
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 2/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ስታርት አፕ አውደ ርዕይ አገሪቱ በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል እምቅ የፈጠራ ሀሳቦች እንዳሏት የተመለከትንበት ነው ሲሉ ጎብኚዎች ተናገሩ። የኢትዮጵያ "ስታርት አፕ" አውደ ርዕይ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በሳይንስ ሙዚየም ለጎብኚዎች ክፍት ሆኗል። አውደ ርዕዩ ከመጋቢት 30 እስከ ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም የሚዘልቅ ሲሆን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በኢንዱስትሪ፣ በፋይናንስና በሌሎች ዘርፍ የተሰማሩ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ''ስታርት አፖች'' ተሳትፈውበታል። በመጀመሪያ ደረጃ የሚገኙ፣ የመጀመሪያ ደረጃን የተሻገሩና ወደ ገበያ የተቀላቀሉ ስታርት አፖች ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል።   አውደ ርዕዩ ስታርት አፖች የእርስ በእርስ ልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ዕድል ከመስጠት አኳያም ያለው ፋይዳ ከፍ ያለ መሆኑም ነው የገለጹት። የአውደ ርዕዩ ጎብኚዎች በተለይ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ አውደ ርዕዩ በስታርት አፕ ዘርፍ ኢትዮጵያ ተስፋ እንዳላት የሚያመላክት መሆኑን ገልጸው፤ እንደ አገር ለጉዳዩ የተሰጠው ትኩረት የሚበረታታ ነው ብለዋል። ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል የስፔስና ጂኦስፓሻል ኢኒስቲትዩት የዳታና የሲስተም አስተዳደር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ጌትነት ገብረእግዚአብሄር፤ በአውደ ርዕዩ አገርን ከችግር የሚያላቅቁ ተስፋ ሰጪ የፈጠራ ሀሳቦችን ማየታቸውን ተናግረዋል።   ስታርት አፖችን ውጤታማ ለማድረግ በመንግሥት እየተተገበሩ የሚገኙ አዳዲስ አሰራሮች የሚበረታቱ ናቸው ያሉት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፤ ስታርት አፖች በቂ ፈንድ አግኝተው ሀሳቦቻቸው ወደ ምርት ደረጃ እስኪያሸጋግሩ ድረስ ዘላቂ ድጋፍ የሚያገኙበት ሁኔታ መፍጠር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል። ስታርት አፖች ሥራዎቻቸውን እንዲያቀርቡ የተዘጋጀው አውደ ርዕይ በርካታ ፋይዳ አለው ያሉት አቶ ጌትነት የስታርት አፕ ሀሳብ ኖሯቸው ወደ ገበያው መውጣት ያልቻሉ ዜጎችን የሚያነሳሳ ነው ብለዋል። የባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር ወንድማገኝ ማሞ በበኩላቸው በአውደ ርዕዩ የቀረቡ የፈጠራ ውጤቶችን የሚያበረታቱ መሆኑን ገልጸው አሁንም ገና ጅምር ላይ በመሆናችን ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት። በተለይም የፈጠራ ሀሳብ ይዘው ወደ መሬት ማውረድ ያልቻሉትን ከያሉበት ፈልጎ ወደ ስታርት አፕ ምህዳር እንዲመጡ ማድረግ ላይ ብዙ መሥራት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል። የባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር እዬቤል ሙሉጌታ በበኩላቸው አውደ ርዕዩ በውጭ ያሉ የፈጠራ ሀሳቦች ኢትዮጵያ ውስጥ መሰራት እንደሚችሉ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።   በተለይም የስታርት አፕ ትግበራ በኢትዮጵያ ትኩረት እያገኘ መምጣቱ እንደ አገር ቁልፍ የሆኑ እንደ ሥራ አጥነት ችግሮችን ለመፍታት አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል።  
መንግስት ለስታርት አፖች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እያከናወናቸው ያሉ ማሻሻያዎች ዘርፉ ይበልጥ እንዲነቃቃ የሚያደርጉ ናቸው
Apr 9, 2024 329
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 1/2016(ኢዜአ)፦ መንግስት ለስታርት አፖች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እያከናወናቸው ያሉ ማሻሻያዎች ዘርፉ ይበልጥ እንዲነቃቃ የሚያደርግ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው ስታርት አፖች ገለጹ፡፡ የኢትዮጵያ "ስታርት አፕ" ኤግዚቢሽን የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ትናንት በሳይንስ ሙዚየም ተከፍቷል።   በኤግዚቢሽኑም በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በኢነርጂ፣ በኢንዱስትሪ፣ በፋይናንስና በሌሎች ዘርፍ የተሰማሩ በመጀመሪያ ደረጃ የሚገኙ፣ የመጀመሪያ ደረጃን የተሻገሩና ወደ ገበያ የተቀላቀሉ ስታርት አፖች የፈጠራ ውጤታቸውን አቅርበዋል። በኤግዚቢሽኑ "እርሻ" የተሰኘ ዲጂታል መተግበሪያ ይዛ የቀረበችው ሜሮን ስለሺ፤ መተግበሪያው አርሶ አደሮችን ከእርሻ ግብዓትና የሜካናይዜሽን አገልግሎት አቅራቢዎች ጋር የሚያገናኝ ነው። እንዲሁም አርሶ አደሮች ተለዋዋጭ የአግሮ-አየር ንብረት ምክር እንዲጠይቁ የሚያስችል ዲጂታል መድረክ ነው ብላለች ። ለዚህ ደግሞ የሞባይል መተግበሪያን ፣ የጥሪ ማዕከል እና ወኪሎችን ያጣመረ መሆኑን ተናግራለች። ስታርት አፖች አዲስ ሃሳብ ይዘው ወደ ማህበረሰቡ ለመግባት ጊዜ እንደሚወስድ ጠቅሳ ፤ መንግስት እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ስታርት አፖችን ለማስተዋወቅ እና የበለጠ እንዲሰሩ የሚያግዝ እንደሆነ ገልፃለች።   የኖሊጋ ኢንጂነሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ኦፕሬሽን ኃላፊ ካሳ ደጀኔ በኤግዚቢሽኑ ከማንኛውም ወራጅ ውሃ ሃይል ማመንጨት የሚያስችል ተርባይን እና ከንፋስ በቀላሉ ሃይል ማመጨት የሚያስችል ፈጠራ ስራ ይዘው መቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡ የፈጠራ ስራዎችን በሚያከናወኑበት ወቅት ከመንግስት የፋይናንስ ድጋፍ ማግኘታቸውን ጠቅሰው፤ በአጠቃላይ በመንግስት የተወሰዱት አዳዲስ የህግ ማሻሻያዎችን ለስታርት አፕ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። የሲምቦና አፍሪካ መስራች ሃና ብርሃኑ በበኩሏ ሲምቦና አፍሪካ በኢትዮጵያ ውስጥ የህክምና መሳሪያዎችን ማምረት ላይ የሚሰራ ሜድቴክ ኩባንያ መሆኑን ተናግራለች።   በኤግዚቢሽኑ ዩ.ቪ.ሲ. ስትራላይዘር መሳሪያ፣ የፎቶ ቴራፒ መሳሪያ፣ የጨቅላ ህፃናት ማሞቂያ ኦክስጅን ይዘው መቅረባቸውን ተናግራለች። እነዚህን ስራዎች በሚያከናውኑበት ወቅት የፋይናስ ችግር ሲያጋጥማቸው እንደነበር ጠቅሳ፤ መንግስት ይህን ለመቅረፍ እያከናወነ ያለው ተግባራት ስታርት አፖችን የሚያበረታታ ነው ብላለች። ባሳለፍነው ሳምንት በዓድዋ መታሰቢያ በተካሄደው “የኢትዮጵያ ስታርት አፕ ብሔራዊ ሁነት” ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "ፈጠራ ላይ የተመሰረተና የመፍትሔ ሃሳብ ያላቸውን ስታርት አፖች መደገፍ ኢንቨስትመንት እንጂ እርዳታ አይደለም" በማለት መልዕክት ማስተላለፋቸው ይታወቃል፡፡ በመድረኩም መንግስት ለስታርት አፖች ምቹ ምህዳር መፍጠር የሚያስችሉ ዘጠኝ የአሰራር ማሻሻያዎችን ይፋ አድርጓል፡፡ ማሻሻያዎቹ ከዚህ ቀደም የነበሩ የአሰራር ማነቆዎችን እንደሚፈቱም ነው የተገለጸው፡፡      
በኢትዮጵያ ለስታርት አፕ ምቹ ምህዳርን ለማስፋት መንግስት በትኩረት እየሰራ ነው- የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)
Apr 8, 2024 449
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 30/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ለስታርት አፕ ምቹ ምህዳርን ለማስፋት መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገለጹ። የኢትዮጵያ ስታርት አፕ ኤግዚቢሽን በሳይንስ ሙዚየም የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተከፍቷል። በመክፈቻ መርሐ ግብሩ ላይ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እና ሌሎች የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።   የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ መንግስት ኢትዮጵያን የስራ ፈጣሪዎች ሀገር ለማድረግ ስታርት አፕ ላይ በትኩረት እየሰራ ይገኛል። ኢትዮጵያ በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በሒሳብና በምህንድስና ችግሮችን መፍታት እና ሃብት መፍጠር የሚችሉ በርካታ ክህሎት ያላቸው ወጣቶች እንዳሏትም ጠቅሰዋል። እነዚህን ወጣቶች የሚደግፍ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር መንግስት ለስታርት አፕ ልዩ ትኩረት ሰጥቷል ነው ያሉት። ይህን መሰረት በማድረግ ከመጋቢት 30 እስከ ሚያዝያ 20/2016 ዓ.ም የሚቆይ ኤግዚቢሽን መከፈቱን ተናግረዋል። ኤግዚቢሽኑ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ሃሳብ ያላቸው ወጣቶች ለሌሎች ተሞክሯቸውን እንዲያጋሩ፣ ጀማሪ ስራ ስታርት አፖችን ለማስተዋወቅ እና የተሻለ ስራዎችን እንዲሰሩ ለማድረግ ያለመ እንደሆነ አስረድተዋል። በስታርት አፕ ውስጥ ያሉ ስራ ፈጣሪዎችን በማብቃት በፖሊሲ እና በፋይናስ በመደገፍ ውጤታማ እንዲሆኑ ለማበረታታት ነው ብለዋል። በኤግዚቢሽኑ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በኢነርጂ፣ በኢንዱስትሪ፣ በፋይናንስና በሌሎች ዘርፎች ችግር የሚፈቱና ውጤት የሚያመጡ የስራ ፈጣሪዎች ሀሳቦችና ምርቶች ለዕይታ መቅረባቸውንም ዶክተር ኢዮብ ገልጸዋል። መንግስት የስታርት አፕ ምቹ ምህዳርን ለማስፋት ፈንድ ማቋቋምን ጨምሮ የተለያዩ ስራዎች እያከናወነ እንደሚገኝም ነው ሚኒስትር ዴኤታው የተናገሩት። ከመንግስት ባሻገር ባለሃብቶች እነዚህን ስታርት አፖች በመደገፍ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል። በኤግዚቢሽኑ የፈጠራ ስራዎቻቸውን ያቀረቡ ስታርት አፖች ኤግዚቢሽኑ ስራዎቻቸውን ለማስተዋወቅ፣ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ እና ትስስር ለመፍጠር እንደሚያግዛቸው ጠቁመዋል። የ''ስታርት አፕ ኢትዮጵያ'' ፎረም ባሳለፍነው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በአደዋ ድል መታሰቢያ መካሄዱ ይታወቃል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት ከለውጡ በፊት በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ ስታርት አፖች ከ50 እንደማይበልጡ ጠቅሰው፣ አሁን ላይ ከ900 በላይ ስታርታ አፖች መኖራቸውን ተናግረዋል። መንግስት በቀጣይ የስታርት አፕ ሀሳቦችን በተደራጀ ህግና አሰራር ሰርዓት ለመደገፍ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል። ወጣቶች የፈጠራ ሃሳባቸውን መውደድ፣ መቻል፣ መፈለግና መሸጥ እንዳለባቸው የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ጥልቅ ፍላጎት፣ ተልእኮ እና ችሎታ ለጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች /ስታርት አፕ/ መሳካት መሰረት መሆናቸውን አብራርተዋል። መንግስት የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ወጣቶች ሃሳባቸውን ወደ ተግባር ለማዋል በሚፈልጉበት ወቅት ያለምንም የንግድ ቤት ኪራይ ውል ሥራ መጀመር የሚችሉበትን አዲስ አሠራር መዘርጋቱን ይፋ አድርጓል። በተጨማሪም ማንኛውም የውጭ ሀገር ፈንድ ያገኘ ስታርት አፕ ሙሉ በሙሉ የውጭ ምንዛሪውን ለሚፈልገው ሥራ ማዋል የሚችልበት አሠራርም ወደ ትግበራ ገብቷል። አዲስ ፈጠራ ያላቸውና ሥራቸውን ወደ ገቢ መቀየር የሚችሉ ወጣቶች በውጭ ሀገራት ለተለያዩ አገልግሎቶች ክፍያ ሲጠየቁ መንግሥት በሚያመቻቸው አሠራር ክፍያ መፈጸም የሚችሉበት አማራጭ የሚመቻችላቸው ሲሆን ይህም ዓለም አቀፋዊ ለሆነው የስታርት አፕ ዘርፍ ምቹ ምሕዳር ይፈጥራል ተብሏል። በሌላ በኩል በፈጠራ ላይ ለተመረኮዙ ቴክኖሎጂ መር ሥራ ፈጣሪዎች በጉምሩክ አሠራር ሂደት የሚያጋጥሙ ክፍያዎችን የሚቀንስና፣ የጉምሩክ ድጋፍ የሚያገኙበት ማዕከል እንደሚቋቋም ተገልጿል።      
የአሜሪካ የትራንስፖርት ደኅንነት አስተዳደር በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ያደረገውን የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ኦዲት በስኬት አጠናቀቀ-የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት
Apr 6, 2024 415
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 28/2016(ኢዜአ)፦ የአሜሪካ የትራንስፖርት ደኅንነት አስተዳደር በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ያደረገው የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ኦዲት በስኬት መጠናቀቁን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ። የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ የአሜሪካ የትራንስፖርት ደኅንነት አስተዳደር (TSA) ከመጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ኦዲት ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ የኦዲት ልዑክ ቡድኑ በቆይታው የመንገደኞች፣ የሻንጣ፣ የካርጎ ጭነቶች፣ የዙሪያ ጥበቃና ፍተሻ እንዲሁም የአውሮፕላን ደኅንነትን ለማረጋገጥ የሚወሰደው የሴኪዩሪቲ እርምጃ ከዓለም አቀፍ አሰራር አንጻር አጠቃላይ ያለበትን ደረጃ በተመለከተ ሁሉን አቀፍ ኦዲት አድርጓል፡፡   በኦዲቱ ጥልቅ የሠነድ ግምገማ እና የአካል ምልከታ የተደረገ ሲሆን፤ በልዑኩ በቀረበው የማጠቃለያ ሪፖርት ወደ አሜሪካ ሀገር በሚደረጉ በረራዎችም ሆነ አጠቃላይ በአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ኦፕሬሽናል ሂደቶች ላይ ምንም ዓይነት የደኅንነት ስጋት እንደሌለ በድጋሚ መረጋገጡ ተገልጿል፡፡ በኢትዮጵያ ጠንካራ የሆነ የኢቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ስርዓት መገንባቱን እንዲሁም በቀጣይም በአፍሪካ ምርጥ የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ለመሆን የተያዘውን ስትራቴጂክ ዕቅድ ለማሳካት የሚያስችል መሰረት እንደተጣለ የትራንስፖርት ደኅንነት አስተዳደር (TSA) ተወካይ ገልጸው በሁለቱ ተቋማት ብሎም ሀገራት መካከል በዘርፉ የሚደረገው ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡ በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የሲቪል አቪዬሽን ደኅንነት ዋና መምሪያ ዳይሬክተር አቶ አስራት ቀጀላ የኦዲት ሪፖርቱ በቀረበበት መርሐ ግብር ባደረጉት ንግግር በአገልግሎት መስሪያ ቤቱ በተሰጠው ልዩ ትኩረት በሲቪል አቪዬሽን ደኅንነት ዋና መምሪያ የተደረገው ሁሉን አቀፍ ሪፎርም፣ የተዘረጋው አሰራር፣ የሰው ኃይል ልማት፣ የቴክኖሎጂ እምርታ እና ከምንጊዜውም በላይ የተጠናከረው የኤርፖርት ባለድርሻ አካላት ቅንጅት የትራንስፖርት ደኅንነት አስተዳደርን (TSA) እና ከዚህ ቀደም የተደረጉ ሌሎች ተከታታይ ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ምዘናዎችን ስኬት ለመጎናፀፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አንደነበራቸው ገልፀዋል፡፡ በኦዲቱም ለተገኘው ሀገራዊ ውጤት ሌት ተቀን ሲተጉ ለነበሩ የዋና መምሪያው ሠራተኞችና አመራሮች እንዲሁም በኤርፖርት ለሚገኙ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በቀጣይም በሚደረገው ሀገራዊ የዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) ኦዲት ሁሉም በከፍተኛ ቅንጅት፣ ቁርጠኝነት እና ትብብር በመስራት ኢትዮጵያን በከፍታ ማስጠራት እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ለሀገራዊ ኦዲቱም ከወዲሁ ስራዎች ተለይተው እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡   የአሜሪካ የትራንስፖርት ደኅንነት አስተዳደር ከሐምሌ 10 እስከ ሐምሌ 12 ቀን 2015 ዓም ድረስ ለተከታታይ ሦስት ቀናት በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ባካሄደው የበረራ ደኅንነት ልዩ ኦዲት በዓለም አቀፍ አሰራር መሰረት ምንም አይነት የደኅንነት ክፍተት (ግኝት) እንደሌለበት መግለጹ ይታወሳል፡፡ የአሜሪካ የትራንስፖርት ደኅንነት አስተዳደር ሐላፊ ዴቪድ ፕኮስኬ የኦዲት ውጤት መገኘቱን ተከትሎ ነሐሴ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በተቋሙ ባደረጉት ጉብኝት ለኢትዮጵያ የበረራ ደኅንነት አጠባበቅ አድናቆታቸውን መግለጻቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙኃን የላከው መረጃ አመልክቷል፡፡ በመጨረሻም በዋና መምሪያው የተጀመረውን ሪፎርም አጠናክሮ በማስቀጠልና በኤርፖርቱ የሚገኙ ሁሉንም በለድርሻ አካላት አቀናጅቶ በማነቃነቅ ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት አሰራሮች ተዘርግተው እየተተገበሩ መሆኑን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጠቁሟል። ተገልጋዩ በኤርፖርቱ ማህበረሰብ ከሚሰጡ አገልግሎቶቾ ጋር በተያያዘ አስተያየትና ቅሬታ ሲኖረው በኤርፖርት ውስጥ በተዘረጋው የአስተያየትና የጥቆማ መስጫ ስርዓት በግልጽ ሀሳቡን በመስጠት የተሻለ አገልግሎቶች ማግኘት እንዲችል በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስታውቋል።
ማዕከሉ የአፍሪካ የካይዘን ፍልስፍና ቴክኖሎጂ የብቃት ማዕከል ለመሆን እየሰራ ነው
Apr 4, 2024 370
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ካይዘን ልህቀት ማዕከል የአፍሪካ የካይዘን ፍልስፍና ቴክኖሎጂ የብቃት ማዕከል ለመሆን እየሰራ መሆኑን ገለጸ። የማዕከሉ ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ምንዳዬ ይርጋ ለኢዜአ እንዳሉት ማዕከሉ የካይዘን ፍልስፍና ቴክኖሎጂዎችን በጥናትና ምርምር አስደግፎ በማስተላለፍ የአምራች ኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪነት ለማሻሻል እየሰራ ነው። በሀገር በቀል ምጣኔ ሃብት ለውጥ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች አንዱ የሆነው የማምረቻው ዘርፍ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን በተለየ ትኩረት እየተሰራበት መሆኑን ተናግረዋል። ማዕከሉ ጥራትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲሁም የአምራችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን የስራ ባህል ለማሻሻል በየአመቱ 150 በሚደርሱ ድርጅቶች ፍልስፍናውን ለማስረጽ እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል። ማዕከሉ የአፍሪካ የካይዘን ፍልስፍና ቴክኖሎጂ ልህቀት ማዕከል ለመሆን እየሰራ እንደሚገኝም ስራ አስኪያጁ አስታውቀዋል። ከጃፓን መንግስት ጋር በመተባበር በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የሚገኙ ተቋማትን በካይዘን ፍልስፍና ቴክኖሎጂ ለማብቃት የሚረዳ ስልጠና ለመስጠት እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል። ማዕከሉ የአፍሪካ ሀገራት የምጣኔ ሃብት ዘርፋቸውን ምርታማና ተወዳዳሪ እንዲያደርጉ ስልጠናዎችን መስጠት የሚያስችል የሰው ሃይልና ዝግጁነት አለው ብለዋል። ማዕከሉ 11 አነስተኛ ማሰልጠኛ ክፍሎች እንዳሉትና በዚህም በአንድ ጊዜ እስከ 440 ሰልጣኞችን ማስተናገድ እንደሚችል ገልጸዋል። በተጨማሪም ዘመናዊ ካፍቴሪያዎች፣ የመኝታ ክፍሎችና ሌሎች አስፈላጊ ግብአቶችን አሟልቶ የተገነባ በመሆኑ በሀገር አቀፍ እንዲሁም አህጉር አቀፍ ደረጃ ስልጠናዎችን የመስጠት ብቃት አለው ብለዋለ። ማዕከሉ በጃፓን መንግስት ድጋፍ ተገንብቶ መስከረም 27 ቀን 2016 ዓ.ም መመረቁ ይታወሳል። የካይዘን ፍልስፍና በጥራት፣ ቦታ አጠቃቀም፣ የሃብት ብክነት፣ ወጭና ሌሎች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ሃብትን በአግባቡ ተጠቅሞ ውጤታማና ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያግዝ ነው።
የ'ስማርት አዳማ' ፕሮጀክት በከተማው አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ለማምጣት አስችሏል-- አቶ ሀይሉ ጀልዴ
Apr 4, 2024 300
አዳማ፣መጋቢት 26/2016(ኢዜአ)የ'ስማርት አዳማ' ፕሮጀክት በከተማው አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ማስቻሉን የከተማው ከንቲባ አቶ ሀይሉ ጀልዴ አስታወቁ። የ'ስማርት አዳማ' ፕሮጀክት የሶስት ዓመት አፈፃፀምና ቀጣይ የዲጂታል አገልግሎት ትግበራን የተመለከተ ውይይት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተካሄዷል።   የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የ'ስማርት አዳማ' ፕሮጀክት የተሻለ ውጤት እየተገኘበት ነው። በተገኘው ውጤትም የኢትዮጵያ ከተሞች የዲጂታል አገልግሎትን ለማስፋፋት ከአዳማ ከተማ ልምድ እየቀሰሙ መሆኑን ተናግረዋል። በ'ስማርት አዳማ' የእስካሁን አፈፃፀም በአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ላይ ለውጥ መምጣቱን ገልጸው በዚህም ብልሹ አሰራርና ሌብነትን ከማስወገድና የህዝቡን ቅሬታ ለመፍታት ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ጠቁመዋል። የ'ስማርት አዳማ' ግብ ዘመናዊና ዲጂታል አገልግሎትን በሁሉም ዘርፎች መተግበር መሆኑን ያስታወሱት ከንቲባው በዚህ ረገድም ዘርፈ ብዙ ስራዎች ተሰርተዋል ነው ያሉት። በተለይም መሬት፣ ገቢዎች፣ ትራንስፖርት፣ ውሃና ፍሳሽ፣ ንግድ፣ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት፣ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት፣ የትራፊክ አገልግሎት፣ የፍትህ እንዲሁም የከተማዋን ሰላም በቴክኖሎጂ ታግዞ ለመጠበቅ ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል። በወቅቱ ሀሳቡ ተግባራዊ መደረግ ሲጀመር ብዙ ችግሮች እንደነበሩ አንስተው አሁን ግን ተጨባጭ ውጤት እየታየበት መሆኑን ተናግረዋል። በኦሮሚያ መሬት ቢሮ የፕላንና ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ይልማ ሲሳይ የ'ስማርት አዳማ' ፕሮጀክት ከተማው በተለይም በመሬት አስተዳደር ዘርፍ ለህብረተሰቡ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ወደ ዘመናዊ አሰራር መቀየር እንዳስቻለ ተናግረዋል። ባለፉት ሶስት ዓመታት ከመሬት አስተዳደር ጀምሮ በተለያዩ ዘርፎች የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን የተሰራው ስራ ውጤት ከማስገኘቱም ባለፈ ለሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ሞዴል እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል። በዚህም መስተዳድሩ ከ519 ሺህ በላይ የመሬት ይዞታ ፋይሎችን ወደ ዲጂታል በማስገባት የቀጥታ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ብለዋል። በአዳማ በዲጂታላይዜሽን አገልግሎት የታየውን ውጤትና ተሞክሮ ከ30 በላይ በሚሆኑ የክልሉ ከተሞችና 124 ወረዳዎች የማስፋፋት ስራ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል። በ23 ዋና ዋና የክልሉ ከተሞች የመሬት ይዞታ የካዳስተር ምዝገባ ስራ ዘንድሮ እንደሚጠናቀቅ የገለጹት አቶ ይልማ በቀጣይ ከወረቀት ንክኪ ነፃ የሆነ ዲጂታል አገልግሎት በሁሉም ከተሞች ተደራሽ የሚደረግ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል። በየደረጃው ባለው የመሬት መዋቅር ውስጥ ያለውን የህዝብ ቅሬታ ከመሰረቱ ለማስወገድ አዳማ ከተማ ላይ የተጀመረውን የዲጂታላይዜሽን የአሰራር ስርዓት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።      
የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ዘርፍን በቴክኖሎጂ ለማዘመን የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ
Apr 4, 2024 253
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2016(ኢዜአ)፦የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲቲዩት የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ዘርፍን በቴክኖሎጂ ለማዘመን የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል። ስምምነቱን የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ደንጌ ቦሩ ከኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲቲዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ይታገሱ ደሳለኝ ጋር ተፈራርመዋል። የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትሩ ዶክተር አለሙ ስሜ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ የአንድ ሀገር የኢኮኖሚ የደም ስር ነው ብለዋል። ስምምነቱ ዘርፉን በቴክኖሎጂ በመደገፍ እና ዘመኑን የዋጀ በማድረግ ውጤታማነቱን እንደሚያሳድግ አመላክተዋል። የተደረገው ስምምነት የሀገር ውስጥ አቅምን በመጠቀም ቴክኖሎጂን በማበልጸግ የሚከናወን መሆኑን ጠቁመዋል። የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ አሰራርን ማዘመን በራሱ ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት ለመስጠት ከማስቻሉ ባለፈ ወደ ብልጽግና የሚደረገውን ጉዞ የሚያፋጥን መሆኑን ተናግረዋል። የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ወርቁ ጋቸና በበኩላቸው ኢንስቲቲዩቱ አገልግሎቶቹን ዲጂታላይዝ በማድረግ ምርታማነት እንዲጨምር የሚያስችሉ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ውጤቶች የአገልግሎት ዘርፉ እንዲዘምን እና እንዲሳለጥ ጉልህ ሚና እንዳላቸው አመላክተዋል። ኢንስቲቲዩቱ በስምምነቱ በመታገዝ የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ዘርፉን የሚያዘምኑና ችግሮችን የሚፈቱ ቴክኖሎጂዎችን በተያዘላቸው ጊዜ ለማቅረብ እንደሚሰራ ተናግረዋል የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ደንጌ ቦሩ ስምምነቱ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተያያዙ ተግዳሮቶችን የሚቀርፍ መሆኑን ገልጸዋል። ስምምነቱ በአጠቃላይ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎችን የሚያቀላጥፍና ውጤታማ በሆነ መልኩ ዘርፉን መምራት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል። የኢንስቲቲዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ይታገሱ ደሳለኝ ስምምነቱ የትራንስፖርት ዘርፉን በቴክኖሎጂ በማዘመን አገልግሎት አሰጣጡን ለማሳለጥ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል። ኢንስቲቲዩቱ በስምምነቱ መሰረት የሚቀርቡለትን ፕሮጀክቶች በፍጥነት በማልማት በተያዘላቸው ጊዜ ለማቅረብ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።    
በኦሮሚያ 82 ስማርት የመማሪያ ክፍሎችን ለማደራጀት የሚያስችል ሥምምነት ተደረገ 
Apr 1, 2024 250
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 23/2016(ኢዜአ)፦ የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ በክልሉ ስማርት የመማር ማስተማር ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችለውን የመግባቢያ ሥምምነት ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር ተፈራረመ። ሥምምነቱን የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶና የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ዛሬ ፈርመውታል። ስምምነቱ ትምህርት በዲጂታል ታግዞ የሚተገበርበትን የስማርት መማር ማስተማር እንዲካሄድ ይረዳል። የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፤ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን በትምህርት ዘርፉም እንዲተገበር በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ ነው። ይህንንም ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል ትምህርትን በዲጂታላይዜሽን የታገዘ እንዲሆንና ስማርት የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማሳለጥ ዛሬ የመግባቢያ ሥምምነት መደረጉን ገልጸዋል። በዚህም በክልሉ በ8 አዳሪ ትምህርት ቤቶችና በ33 ልዩ ትምህርት ቤቶች በአጠቃላይ 82 ስማርት የመማሪያ ክፍሎችን አሟልቶ ለማቅረብ የተደረገ ሥምምነት መሆኑን ተጠቁሟል። የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በበኩላቸው: ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የትምህርት መስኩ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል። በመሆኑም ዘመኑ ያፈራቸውን ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የትምህርት አሰጣጥ ሥርዓቱን ጥራት ያለው ፍትኃዊና አካታች የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፈን ትኩረት ተደርጎ ይሰራል ነው ያሉት።  
በአዲስ አበባ የሚሰጠው የመሬት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል ተሸጋግሯል
Apr 1, 2024 263
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 23/2016(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ የሚሰጠው የመሬት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል መሸጋገሩን የአዲስ አበባ መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ ። የቢሮው ኃላፊ አቶ ሲሳይ ጌታቸው ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ ቢሮው ለአገልግሎት ፈላጊዎች ዘመናዊ እና የተሳለጠ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅትም 700 ሺህ ፋይሎች ወደ ዲጂታል መቀየራቸውን ገልጸው 'ሰርቨር' ላይ መጫኑንም አስረድተዋል። 16 አገልግሎቶችን ደግሞ ሙሉ በሙሉ በኦንላይን መስጠት የተጀመረ በመሆኑ ደንበኞች ካሉበት ቦታ አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ አብራርተዋል። ከወሳኝ ኩነት፣ ቴሌ ብርና ሌሎች መሰል አገልግሎት ሰጪዎች ጋር በመቀናጀት ለደንበኞች የተሻለ አገልግሎት በመስጠት እርካታውን ለመጨመር ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ብለዋል ። ቢሮው 'ቴኑዩር ኢንፎርሜሽን አስተዳደር ሲስትም አልምቶ' ስራ ላይ ማዋሉን ገልጸው፤ አሰራሩ ለዜጎች የተደራጀ አገልግሎት በመስጠት ውጤታማ የሚያደርግ መሆኑን አብራርተዋል።    
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የኢትዮ ቴሌኮም ኩባንያን ጎበኙ
Mar 31, 2024 261
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 22/2016(ኢዜአ)፦ በቅርቡ የኢትዮ ቴሌኮም የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው የተሰየሙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከቦርዱ አባላት ጋር በመሆን በኩባንያው የተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወር ጉብኝት አድርገዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና የቦርድ አባላቱ ጉብኝታቸውን በአድዋ የድል መታሰቢያ በሚገኘው የኩባንያው ኤክስፒሪየንስ ማዕከል በመጀመር በፕሪሚየም አገልግሎት ማዕከል፣ ሞጁላር ዳታ ሴንተር እና የደንበኞች አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ጎብኝተዋል። በጉብኝቱ ወቅት ኩባንያው የኮኔክቲቪቲ ተደራሽነት እና ጥራት ከማሻሻል ባሻገር የዲጂታል ሶሉሽኖችን እና የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን በማቅረብ የህዝብን ህይወት ለማቅለል በርካታ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በቴሌኮም እና በዲጂታል መሠረተ ልማት አቅም የተፈጠረውን አስቻይ ሁኔታ በመጠቀም የመንግስት ተቋማት አሰራሮቻቸውን በዲጂታል በማዘመን ፈጣን፣ ቀልጣፋና አስተማማኝ አገልግሎት ማቅረብ እንዲችሉ የተገነቡ የዲጂታል አቅሞችን እንዲያውቁት እና እንዲጠቀሙበት ማድረግ እንደሚገባ አጽንኦት ተሰጥቷል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም የዲጂታል ኢትዮጵያን ጉዞ ዕውን ለማድረግ እያደረገ ያለውን ጥረት እና አስተዋጽኦ በማድነቅ ይህ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቦርዱ ተገቢውን ድጋፍ እና አመራር እንደሚሰጥ መገለፁን ከኩባንያው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም