የኢትዮጵያ የግብርና ምርት በዓለም ገበያ ያለውን ተወዳዳሪነት የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎችን የፈጠሩ ስታርት አፖች

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 3/2016(ኢዜአ)፦በስታርት አፕ ኢትዮጵያ አውደ ርዕይ የግብርና ምርትን እሴት በመጨመር በዓለም ገበያ ያለውን ተወዳዳሪነት የሚጨምሩ የፈጠራ ስራዎች ለዕይታ ቀርበዋል።

የወጣቶችን የስራ ፈጠራ ለማስተዋወቅ መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም በተከፈተው በዚህ አውደ ርዕይ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በኢንዱስትሪ፣ በፋይናንስና በሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ''ስታርት አፖች'' እየተሳተፉ ነው።

ከነዚህም መካከል ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልካቸውን የግብርና ምርቶች እሴት በመጨመርና የተደራጀ መረጃ ለገዥዎች በማቅረብ ገቢን ለመጨመር የሚያግዙ የፈጠራ ስራዎችን ያቀረቡ ወጣቶች ይገኙበታል።

ወጣት ሚኪያስ እስጢፋኖስ በኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው የቡና ምርት መረጃን ገዥው መከታተል የሚችልበት "ትሬሲንግ ኮፊ" የተሰኘ ቴክኖሎጂን አቅርቧል።

ይህ ቴክኖሎጂ ከአምራቹ ጀምሮ የቡናን አጠቃላይ መረጃ ገዥው እንዲያውቅ የሚያደርግ ነው ብሏል።

በዚህም የኢትዮጵያ ቡና ልዩነቱና ጥራቱ የተረጋገጠ ስለመሆኑ ግልፅ መረጃ ለገዥዎች በመስጠት በዓለም ገበያ ያለውን ተወዳዳሪነት የበለጠ ማሳደግ የሚያስችል መሆኑን አብራርቷል።

የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያና የእርሻ ማሽኖችን የሚያመርተው የ"ግሪን ቢን ማኑፋክቸሪንግ" ስራ አስኪያጅ አንዱዓምላክ መሃሪው፥ የወጪ ንግድ ምርቶችን እሴት ለመጨመር ጥቅም ላይ የሚውሉ የፈጠራ ስራዎችን አቅርቧል።


 

ቴክኖሎጂው የግብርና ምርትን እሴት ጨምሮ በመላክ ገቢንና ተወዳዳሪነትን ለመጨመር የሚያግዝ መሆኑን አብራርቷል።

የአዝመሪኖ፣ እርድና ቡና ማድረቂያና መቁያ ማሽኖች ከፈጠራ ስራዎቹ መካከል እንደሚገኙበትም ጠቅሷል።

የ"ቢፋርም ቴክ" መስራችና ስራ አስኪያጅ በጋሻው መብራቴ በተመረቀበት የግብርና ሙያ በተለያዩ ተቋማት ተቀጥሮ ሲሰራ ያስተዋለው የግብርና ቴክኖሎጂ እጥረት ለፈጠራ ስራው መነሻ እንደሆነው ተናግሯል።

አርሶ አደሩን ከእህል መውቂያ ትራክተር ባለቤቶች እንዲሁም የትራክተር ኦፕሬተር ሙያተኞች ጋር የሚያገናኝ ቴክኖሎጂ እንደፈጠረ አብራርቷል።


 

ይህም የግብርና ስራን ለማዘመን በሚደረገው ጥረት የራሱን አስተዋጽኦ ለማድረግ እንደሚያግዘው በመጠቆም፥ መንግስት ለፈጠራ ስራ የሰጠው ትኩረት ውጤታማ ለመሆን ተስፋ እንደሰጠው አንስቷል።

የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎቹ እንደገለጹት፥ በአውደ ርዕዩ መሳተፋቸው ከባለሃብቶች፣ ፋይናንስ ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የመገናኘት እድልን ፈጥሮላቸዋል።

የኢትዮጵያ "ስታርት አፕ" አውደ ርዕይ እስከ ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን የመጀመሪያ ደረጃ፣ የመጀመሪያ ደረጃን የተሻገሩና ወደ ገበያ የመቀላቀል ደረጃ ላይ የደረሱ ስታርት አፖች ስራዎቻቸውን አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ ሃሳብ ያላቸው ወጣቶች ለዲጂታል ምጣኔ ሃብት ግንባታ፣ ለስራ ፈጠራ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እንዲያውሉ መንግስት በፖሊሲ ደረጃ ልዩ ትኩረት ሰጥቷል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም