ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የስታርት አፕ ኢትዮጵያ አውደ ርዕይን ጎበኙ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 3/2016(ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሳይንስ ሙዚየም በተከፈተው የ'ስታርት አፕ' ኢትዮጵያ አውደ ርዕይ እየተሳተፉ የሚገኙ ስታርት አፖችን ጎበኙ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት በሳይንስ ሙዚየም እየታየ ያለው የ'ስታርት አፕ' ኢትዮጵያ አውደ ርዕይ በዘርፉ ያሉ ተሳታፊዎችን ተምኔት፣ የፈጠራ ምናብ ስፋት ብሎም ችሎታ ማሳያዎች የቀረቡበት ነው ብለዋል።

በመሆኑም ሁላችሁም አውደ ርዕዩን በመመልከት ከተሳታፊዎቹ ጋር እንድትወያዩ እጋብዛለሁ ሲሉም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ያቀረቡት።

በአውደ ርዕዩ እየተሳተፉ የሚገኙ ስታርት አፖች፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ስራዎቻቸውን በመመልከት እንዳበረታቷቸው ተናግረዋል።

የፕላስቲክ ቆሻሻን ወደ ተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ምርቶች በመቀየር ላይ የተሰማራው የኩቢክ ስታርት አፕ ተወካይ ኤዶም ዳዊት፥ ኩቢክ የፕላስቲክ ቆሻሻን በመሰብሰብ በአነስተኛ ወጪ የሚገነቡ ቤቶችን ለመስራት የሚያገለግሉ ቁሶችን ወደ ማምረት መሸጋገሩን ገልጻለች።


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በአውደ ርዕዩ ተገኝተው ስራዎቻቸውን እንደተመለከቱ የጠቀሰችው ወጣት ኤዶም፥ መንግስት ስታርት አፖችን ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት እንዳረጋገጡም ተናግራለች።

በኤሌክትሪክ ለሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ሃይል የማቅረብ ዓላማ ይዞ የተነሳው ኢትዮ ቻርጅ የተሰኘው ስታርት አፕ ተወካይ ወጣት አብዱ ጀማል፥ የሃይል መሙያ መሰረተ ልማቶችን በሙከራ ደረጃ መትከል መጀመራቸውን ጠቁሟል።


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በኤግዚቢሽኑ ተገኝተው እንዳበረታቷቸው የጠቀሰው ወጣት አብዱ፥ መንግስት ለስታርት አፖች የፖሊሲ እርምጃዎችን በመውሰድ፣ ኤግዚቢሽኖችን በማዘጋጀት ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ገልጿል።

የኢኔብለር ቴክ ተባባሪ መስራች እና ዋና ስራ አስፈጻሚ ይድነቃቸው ከድር፥ የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ስርዓት የሚያዘምን በተገልጋይ ቤተሰብና በአገልግሎት ሰጪው መካከል እንግልትን የሚቀርፍ ስርዓት ይዘው መምጣታቸውን አስረድቷል።


 

በሳይንስ ሙዚየም የተከፈተው አውደ ርዕይ ስታርት አፖች እርስ በርስ እንዲተዋወቁና ልምድ እንዲካፈሉ፣ ከድርጅቶች ጋር ትስስር እንዲፈጥሩ ምቹ ምህዳር እንደሆነላቸውም አንስቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና መንግስታቸው ፈታኝ የሆነውን የስታርት አፕ ምቹ ምህዳርን የመፍጠር ሂደት በቁርጠኝነት መጀመራቸው ለስታርት አፖች ትልቅ ምዕራፍ መክፈቱንም ገልጿል።

ስታርት አፖቹ በቀጣይ ወደ ሙሉ ምርት እና አገልግሎት በመግባት ራሳቸውንና ሀገራቸውን ለመለወጥ በትጋት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ለአብነትም ኢትዮ ቻርጅ የስራ አድማሱን በማስፋት በቀጣይ በሆቴሎች፣ በነዳጅ ማደያዎችና ሌሎች አመቺ ስፍራዎች መሰረተ ልማቱን ለመትከል እቅድ የያዘ ሲሆን አገልገሎቱን ከሰሃራ በታች ሀገራት እንደሚያስፋፋ ገልጿል።

ኢኔብለር ቴክ ደግሞ የአገልግሎት መስመሮችና እና የኃይል ቆጣሪዎችን ክላውድ ቤዝድ ስርዓትን በመጠቀም ለማዘመንና በአገልግሎት ሰጪና በተጠቃሚ ቤተሰብ መካከል ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር እየሰራ ነው ብሏል።

ኩቢክ ስታርት አፕ በበኩሉ በኢትዮጵያ ደረጃ የጀመረውን ቆሻሻን የማስወገድ፣ የአካባቢ ጥብቃን የማጎልበት እንዲሁም ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ የማዋል ስራውን አህጉራዊ የማድረግ ህልሙን በአጭር ጊዜ እንደሚያሳካው ነው የጠቆመው።

መንግስት ለስታርት አፕ ምቹ ምህዳርን ለመፍጠር የፖሊሲ እርምጃዎችን ይፋ አድርጎ ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል።

የስታርት አፕ ኢትዮጵያ አውደ ርዕይ ከመጋቢት 30 እስከ ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በኢንዱስትሪ፣ በፋይናንስና በሌሎች ዘርፍ የተሰማሩ ስታርት አፖች እየተሳተፉበት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም