መንግስት ለሰውሰራሽ አስተውሎት ተገቢውን የፋይናንስና የፖሊሲ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል - ገንዘብ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 2/2016(ኢዜአ)፦ መንግስት ለሰውሰራሽ አስተውሎት ተገቢውን የፋይናንስና የፖሊሲ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የኢትዮ-ቴሌኮም 5ጂ ቴክኖሎጂን በመጠቀምና በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በቋንቋ ቅንብር አማርኛ ቋንቋ የምትናገር  ''ደስታ'' ሮቦት  በአይኮግ ላብስ ለምታ በሳይንስ ሙዚየም ለእይታ ቀርባለች።


 

የደስታ ሮቦትን ጨምሮ በስታርት አፕ ኤግዚቢሽን የቀረቡ ስራዎችን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እየጎበኟቸው ነው።

በዚህ ወቅት የገንዘብ ሚኒስቴር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እንዳሉት በዓለም ላይ አዲስ የሆነውን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ ለመጠቀም መንግስት የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ተቋም አቋቁሞ እየሰራ ይገኛል።

ኢንስቲትዩቱም በጤና፣ ግብርናና በሌሎች የተለያዩ ዘርፎች ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም ተጨማሪ አቅም እየፈጠረ እንደሆነም ተናግረዋል።

የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ትኩረት ከሰጣቸው ከአምስቱ የልማት ምሰሶዎች አንዱ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው የሰው ሰራሽ አስተውሎትም በዚህ ስር የሚመደብ መሆኑን ገልፀዋል።

መንግስት ለሰው ሰራሽ አስተውሎት ተገቢውን የፋይናንስና የፖሊሲ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት  የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ተስፋዬ ዘውዴ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ችግሮችን ለመፍታት እንዲያስችሉ ከሚሰራቸው ቴክኖሎጂዎች መካከል ሮቦቲክ ቴክኖሎጂ አንዱ ነው።


 

በኢንስቲትዩቱ በተለያዩ  የአገርኛ ቋንቋዎች መናገር የሚችሉ ሮቦቶች ተሰርተው ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆኑን አንስተዋል።

ከዚህ ቀደም የማሽን ቋንቋ ስላልነበር የአገር ውስጥ ቋንቋዎች ሳይንሳዊ ምርምሮችን ለማድረግና ችግሮችን ለመፍታት እገዛ ሳያደርጉ መቆየታቸውን  ጠቅሰዋል።

አሁን ላይ ኢንስቲትዩቱ በተፈጥሮ ቋንቋ ቅንብር አራት የአገር ውስጥ ቋንቋዎችን ወደ ማሽን ማስገባት ችሏል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ።

ደስታ ሮቦትም በቋንቋ ቅንብር አማርኛን ተጠቅማ ታዳጊዎችና ህፃናት ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ለማነሳሳት ታስባ መቅረቧን ተናግረዋል።

የአይኮግላብ ዋና አማካሪ ቤተልሄም ደሴ በበኩላቸው የደስታ ሮቦት ለእይታ መቅረቧ ህፃናትና ወጣቶች መሰል ስራዎችን እንዲሰሩ ለማበረታታት የሚያስችል እንደሆነ ተናግረዋል።


 

የደስታ ሮቦትን ጨምሮ የተለያዩ የስታርትአፕ አውደ ርዕይ በቀረበበት በሳይንስ ሙዚየም ሲጎበኙ ያገኘናቸው አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው ኤግዚቢሽኑ ህፃናትና ታዳጊዎች ኢትዮጵያ በሳይንስ ዘርፍ የደረሰችበትን እንዲረዱ የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።


 

ደስታ ሮቦት በዛሬው እለት በሳይንስ ሙዚየም ከምታደርገው ቆይታ ባለፈ በነገው እለት ከአርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ ጋር የጃዝ ምሽት እንደሚኖራት ተገልጿል።

በመጪው አርብ ደግሞ በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ከሌሎች በኢንስቲትዩቱ ከተሰሩ ሮቦቶች ጋር ለዕይታ እንደምትቀርብ ተጠቁሟል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም