ስታርት አፖች ለኢትዮጵያ እድገት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ የሚደረጉ ድጋፎች ሊጠናከሩ ይገባል

362

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 5/2016(ኢዜአ)፦ ስታርት አፖችን ለማጠናከርና ለኢትዮጵያ እድገት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ የሚደረጉ ድጋፎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ  ጥሪ ቀረበ። 

ከመጋቢት 30 እስከ ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆየው የኢትዮጵያ "ስታርት አፕ" አውደ-ርዕይ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በሳይንስ ሙዚየም ለጎብኚዎች ክፍት ተደርጓል።      

በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በኢንዱስትሪ፣ በፋይናንስና በሌሎች ዘርፍ የተሰማሩ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ''ስታርት አፖች'' በአውደ-ርዕዩ በመሳተፍ ላይ ናቸው። 


 

አውደ-ርዕዩ የተዘጋጀው በአገሪቱ የሚገኙ ስታርት አፖች ያላቸውን ምርትና አገልግሎት እንዲሁም ፈጠራዎች ተደራሽ ማድረግ ነው።   

ኢዜአ ያነጋገራቸው በአውደ-ርዕዩ የተሳተፉ፤ ስታርት አፖች ለኢትዮጵያ እድገትና ብልጽግና የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ለዘርፉ የሚደረጉ ዘርፈ-ብዙ ድጋፎች መጠናከር እንዳለባቸው ይናገራሉ።  

ቴክኖሎጂ አልሚዎችን ከገበያው ጋር ለማገናኘት የሚሰራው የኢቴክ ቴክኖሎጂ የማርኬቲንግና የሪሌሽንሺፕ ቺፍ ኦፊሰር እስጢፋኖስ ብርሃኑ፤ ድርጅታቸው አጠቃላይ የቴክኖሎጂ አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሷል። 

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አምና በተዘጋጀ ውድድር ከ90 ስታርት አፖች ተመርጠው ወደ ሞሮኮ ከተጓዙት መካከል መሆናቸውን ጠቅሶ፤ ቴክኖሎጂን በአውትሶርሲንግ (በሦስተኛ ወገን) የሚያሰራ አይ ቲኦ የሚባል ቴክኖሎጂ ማቅረባቸውን ያነሳል። 

አሁን ላይ ለስታርት አፕ የተሰጠው ትኩረት በዘርፉ የተሰማሩ ወጣቶች አቅማቸውን ለማጎልበትና ለአገሪቱ እድገት አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ የሚያግዝ መሆኑን ገልፆ፤ ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግሯል።  

የማሜ መጫወቻዎችና ፐዝሎች መሥራች ዘሩባቤል መስፍን በበኩሉ፤ በቴክኖሎጂው የቀረቡት ፊደል እያንዳንዱ ፊደል በድምፅ የሚያስተምር፣ ቁጥሮችንና አባታዊ ምክሮች ብሎም ሙዚቃዎችና ግጥሞች ያካተተ ነው። 

በሳይንስ ሙዚየም እየተካሄደ ያለው አውደ-ርዕይ ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅና ከደንበኞች ጋር ለመገናኘት እንደሚጠቅም ገልፆ፤ ከሌሎች መሰል ስታርት አፖች ጋር የልምድ ልውውጥ ለማድረግም ያግዛል ብሏል።

የሚሰራበትን ቴክኖሎጂውን ለማበልፀግ አንዳንድ ግብዓቶች ከውጭ የሚመጡ መሆኑን ገልፆ፤ ቀደም ሲል በግብዓቶች ላይ የሚጣለው ቀረጥ ከፍተኛ እንደነበርና አሁን ላይ የዋጋ ቅናሽ መደረጉ የሚበረታታ ነው ብሏል።

በዚህ ረገድ ያሉት የማሻሻያ ሥራዎች ይበልጥ ሊጠናከሩ ይገባል ነው ያለው።


 

አሁን ላይ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን የሚሰራው ኢኔብለር ቴክ መሥራችና ሥራ አስፈጻሚ ይድነቃቸው ከድር በበኩሉ፤ መንግሥት የስታርት አፖች ምህዳሩን ምቹ ለማድረግ የሚሰራቸው ሥራዎች የሚበረታታና ሊጠናከር የሚገባው ነው ብሏል። 

ስታርት አፖች ሥራቸውን ይዘው የሚያቀርቡባቸው ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ መድረኮች የበለጠ አዳዲስ ኃሳብ እንዲያፈልቁ የሚያግዙ እንደሆኑም ተናግረዋል። 

ስታርት አፖች ለተለያዩ አገራት እድገት አስተዋጽዖ ማድረጋቸውን ጠቅሰው፤ በኢትዮጵያም ሚናቸውን እንዲወጡ የባለኃብቶች ድጋፍ ወሳኝ መሆኑንም ገልፀዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም