የኢትዮጵያ ስታርት አፕ አውደ ርዕይ አገሪቱ  በዘርፉ ያላትን እምቅ አቅም ያመላከተ ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 2/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ስታርት አፕ አውደ ርዕይ አገሪቱ  በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል እምቅ የፈጠራ ሀሳቦች እንዳሏት የተመለከትንበት ነው ሲሉ ጎብኚዎች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ "ስታርት አፕ" አውደ ርዕይ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በሳይንስ ሙዚየም ለጎብኚዎች ክፍት ሆኗል።    

አውደ ርዕዩ ከመጋቢት 30 እስከ ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም የሚዘልቅ ሲሆን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በኢንዱስትሪ፣ በፋይናንስና በሌሎች ዘርፍ የተሰማሩ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ''ስታርት አፖች'' ተሳትፈውበታል።    

በመጀመሪያ ደረጃ የሚገኙ፣ የመጀመሪያ ደረጃን የተሻገሩና ወደ ገበያ የተቀላቀሉ ስታርት አፖች ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል።   


 

አውደ ርዕዩ ስታርት አፖች የእርስ በእርስ ልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ዕድል ከመስጠት አኳያም ያለው ፋይዳ ከፍ ያለ መሆኑም ነው የገለጹት።   

የአውደ ርዕዩ ጎብኚዎች በተለይ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ አውደ ርዕዩ በስታርት አፕ ዘርፍ ኢትዮጵያ ተስፋ እንዳላት የሚያመላክት መሆኑን ገልጸው፤ እንደ አገር ለጉዳዩ የተሰጠው ትኩረት የሚበረታታ ነው ብለዋል።  

ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል የስፔስና ጂኦስፓሻል ኢኒስቲትዩት የዳታና የሲስተም አስተዳደር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ጌትነት ገብረእግዚአብሄር፤ በአውደ ርዕዩ አገርን ከችግር የሚያላቅቁ ተስፋ ሰጪ የፈጠራ ሀሳቦችን ማየታቸውን ተናግረዋል።  


 

ስታርት አፖችን ውጤታማ ለማድረግ በመንግሥት እየተተገበሩ የሚገኙ አዳዲስ አሰራሮች የሚበረታቱ ናቸው ያሉት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፤  ስታርት አፖች በቂ ፈንድ አግኝተው ሀሳቦቻቸው ወደ ምርት ደረጃ እስኪያሸጋግሩ ድረስ ዘላቂ ድጋፍ የሚያገኙበት ሁኔታ መፍጠር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።       

ስታርት አፖች ሥራዎቻቸውን እንዲያቀርቡ የተዘጋጀው አውደ ርዕይ በርካታ ፋይዳ አለው ያሉት አቶ ጌትነት የስታርት አፕ ሀሳብ ኖሯቸው ወደ ገበያው መውጣት ያልቻሉ ዜጎችን የሚያነሳሳ ነው ብለዋል።

የባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር ወንድማገኝ ማሞ በበኩላቸው በአውደ ርዕዩ የቀረቡ የፈጠራ ውጤቶችን የሚያበረታቱ መሆኑን ገልጸው አሁንም ገና ጅምር ላይ በመሆናችን ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት።  

  

በተለይም የፈጠራ ሀሳብ ይዘው ወደ መሬት ማውረድ ያልቻሉትን ከያሉበት ፈልጎ ወደ ስታርት አፕ ምህዳር እንዲመጡ ማድረግ ላይ ብዙ መሥራት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

የባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር እዬቤል ሙሉጌታ በበኩላቸው አውደ ርዕዩ በውጭ ያሉ የፈጠራ ሀሳቦች ኢትዮጵያ ውስጥ መሰራት እንደሚችሉ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።    


 

በተለይም የስታርት አፕ ትግበራ በኢትዮጵያ ትኩረት እያገኘ መምጣቱ እንደ አገር ቁልፍ የሆኑ እንደ ሥራ አጥነት ችግሮችን ለመፍታት አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል። 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም