በኢትዮጵያ ለስታርት አፕ ምቹ ምህዳርን ለማስፋት መንግስት በትኩረት እየሰራ ነው- የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 30/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ለስታርት አፕ ምቹ ምህዳርን ለማስፋት መንግስት  በትኩረት እየሰራ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ ስታርት አፕ ኤግዚቢሽን በሳይንስ ሙዚየም የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተከፍቷል። 

በመክፈቻ መርሐ ግብሩ ላይ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እና ሌሎች የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል። 


 

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ መንግስት ኢትዮጵያን የስራ ፈጣሪዎች ሀገር ለማድረግ ስታርት አፕ ላይ በትኩረት እየሰራ ይገኛል።

ኢትዮጵያ በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በሒሳብና በምህንድስና ችግሮችን መፍታት እና ሃብት መፍጠር የሚችሉ በርካታ ክህሎት ያላቸው ወጣቶች እንዳሏትም ጠቅሰዋል።

እነዚህን ወጣቶች የሚደግፍ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር መንግስት ለስታርት አፕ ልዩ  ትኩረት ሰጥቷል ነው ያሉት።

ይህን  መሰረት በማድረግ ከመጋቢት 30 እስከ ሚያዝያ 20/2016 ዓ.ም የሚቆይ ኤግዚቢሽን መከፈቱን ተናግረዋል።

ኤግዚቢሽኑ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ሃሳብ ያላቸው ወጣቶች ለሌሎች ተሞክሯቸውን እንዲያጋሩ፣ ጀማሪ ስራ ስታርት አፖችን ለማስተዋወቅ እና የተሻለ ስራዎችን እንዲሰሩ ለማድረግ ያለመ እንደሆነ አስረድተዋል።

በስታርት አፕ ውስጥ ያሉ ስራ ፈጣሪዎችን በማብቃት በፖሊሲ እና በፋይናስ በመደገፍ ውጤታማ እንዲሆኑ ለማበረታታት ነው ብለዋል።

በኤግዚቢሽኑ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በኢነርጂ፣ በኢንዱስትሪ፣ በፋይናንስና በሌሎች ዘርፎች ችግር የሚፈቱና ውጤት የሚያመጡ የስራ ፈጣሪዎች ሀሳቦችና ምርቶች ለዕይታ መቅረባቸውንም ዶክተር ኢዮብ ገልጸዋል።

መንግስት የስታርት አፕ ምቹ ምህዳርን ለማስፋት ፈንድ ማቋቋምን ጨምሮ የተለያዩ ስራዎች እያከናወነ እንደሚገኝም ነው ሚኒስትር ዴኤታው የተናገሩት።

ከመንግስት ባሻገር  ባለሃብቶች እነዚህን ስታርት አፖች በመደገፍ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በኤግዚቢሽኑ የፈጠራ ስራዎቻቸውን ያቀረቡ ስታርት አፖች  ኤግዚቢሽኑ ስራዎቻቸውን ለማስተዋወቅ፣ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ እና ትስስር ለመፍጠር እንደሚያግዛቸው ጠቁመዋል።

የ''ስታርት አፕ ኢትዮጵያ'' ፎረም ባሳለፍነው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በአደዋ ድል መታሰቢያ መካሄዱ ይታወቃል።

 ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት ከለውጡ በፊት በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ ስታርት አፖች ከ50 እንደማይበልጡ ጠቅሰው፣ አሁን ላይ ከ900 በላይ ስታርታ አፖች መኖራቸውን ተናግረዋል።

መንግስት በቀጣይ የስታርት አፕ ሀሳቦችን በተደራጀ ህግና አሰራር ሰርዓት ለመደገፍ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል።


ወጣቶች የፈጠራ ሃሳባቸውን መውደድ፣ መቻል፣ መፈለግና መሸጥ እንዳለባቸው የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ጥልቅ ፍላጎት፣ ተልእኮ እና ችሎታ ለጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች /ስታርት አፕ/ መሳካት መሰረት መሆናቸውን አብራርተዋል።

መንግስት የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ወጣቶች ሃሳባቸውን ወደ ተግባር ለማዋል በሚፈልጉበት ወቅት ያለምንም የንግድ ቤት ኪራይ ውል ሥራ መጀመር የሚችሉበትን አዲስ አሠራር መዘርጋቱን ይፋ አድርጓል።

በተጨማሪም ማንኛውም የውጭ ሀገር ፈንድ ያገኘ ስታርት አፕ ሙሉ በሙሉ የውጭ ምንዛሪውን ለሚፈልገው ሥራ ማዋል የሚችልበት አሠራርም ወደ ትግበራ ገብቷል።

አዲስ ፈጠራ ያላቸውና ሥራቸውን ወደ ገቢ መቀየር የሚችሉ ወጣቶች በውጭ ሀገራት ለተለያዩ አገልግሎቶች ክፍያ ሲጠየቁ መንግሥት በሚያመቻቸው አሠራር ክፍያ መፈጸም የሚችሉበት አማራጭ የሚመቻችላቸው ሲሆን ይህም ዓለም አቀፋዊ ለሆነው የስታርት አፕ ዘርፍ ምቹ ምሕዳር ይፈጥራል ተብሏል።

በሌላ በኩል በፈጠራ ላይ ለተመረኮዙ ቴክኖሎጂ መር ሥራ ፈጣሪዎች በጉምሩክ አሠራር ሂደት የሚያጋጥሙ ክፍያዎችን የሚቀንስና፣ የጉምሩክ ድጋፍ የሚያገኙበት ማዕከል እንደሚቋቋም ተገልጿል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም