የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ውጤቶችን በመደገፍ  በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የላቀ ውጤት እንዲመዘገብ እየተሰራ ነው -ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 4/2016(ኢዜአ)፦ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ውጤቶችን በመደገፍ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የላቀ ውጤት እንዲመዘገብ እየተሰራ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

"ደስታ" የተሰኘችው ሮቦት ከአንጋፋው የጃዝ ሙዚቃ ባለሙያ ሙላቱ አስታጥቄ ጋር በመሆን የሙዚቃ ትእይንት ትላንት  ምሽት በአዲስ አበባ  አቅርባለች።


  

በመርኃ-ግብሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣የሥራ ፈጠራና ቴክኖሎጂ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስና ቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ትኩረት ስጥታ እየሰራች ነው፡፡  


 

አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ  የዓለም የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይ በኢትዮጵያም ሆነ በአህጉሪቷ የሚስተዋሉ ውስብስብ ችግሮችን ለመፍታት ሁነኛ መፍትሄ እንደሚሆንም ነው የገለጹት፡፡

በመሆኑም መንግስት የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት በማቋቋም ጭምር አርቴፊሻል ኢንተሌጀንስና ሌሎች የዲጂታል አማራጮችን ለማጠናከር በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይህንንም ተከትሎ እንደ "ደስታ" ያሉ የሰው ሰራሽ አስተውሎቶችን በመፍጠር ለዲጂታል ትራስፎርሜሽን ግንባታ የሚሰጠው ትኩረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። 


 

የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተሌጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና በበኩላቸው፣የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እንደ ሀገር የተጀመረውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን በማገዝ በዘርፈ ብዙ  መስኮች ላይ ለመጠቀም የሚያስችል ነው ብለዋል።

በዚህም ፣በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣በኢንዳስትሪ ፓርኮችና ሌሎችም ዘርፎች የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ  በመጠቀም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ እንድትሆን እየተሰራ ነው ብለዋል።

"ደስታ" ሮቦት የሙዚቃ ትዕይንት መርኃ ግብር እንድታሰናዳ የተደረገው የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስና አይኮግ ላብስ ከኢትዮጵያ አየር መንገድና ኢትዮ-ቴሌኮም ጋር በመተባበር ነው። 

ደስታ ሮቦት የአማርኛ ቋንቋን ለመናገር የሚያስችል ፕሮግራም የተጫነላት ሲሆን በመርኃ ግብሩ  በአማርኛ ንግግር አሰምታለች።

የኢትዮ-ቴሌኮም 5ኛ ትውልድ ቴክኖሎጂን በመጠቀምና በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በቋንቋ ቅንብር አማርኛ ቋንቋ የምትናገረው ''ደስታ'' በአይኮግ ላብስ እንደለማች ነው የተገለጸው፡፡

ደስታ የአማርኛ ቋንቋን የምትናገር፣ የግርምት፣ ደስታና ሌሎች ስሜቶችን የምታንጸባርቅ ብሎም መደነስ የምትችል ሮቦት ናት። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም