ኢትዮጵያ ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የሰጠችው ትኩረት ተጠናክሮ ይቀጥላል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 3/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለአርቴፊሻል ኢንተለጀንስና ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የሰጠችው ትኩረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለፁ።

ደስታ የተሰኘችው ሮቦት በስካይ ላይት ሆቴል ከአንጋፋው የጃዝ ሙዚቃ ባለሙያ ሙላቱ አስታጥቄ ጋር በመሆን ሙዚቃዋን ዛሬ ምሽት ታቀርባለች።

በመርኃ-ግብሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሥራ ፈጠራና ቴክኖሎጂ ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

አቶ ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በአርቴፊሻል ኢንትለጀንስና በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ በትኩረት እየሰራች ነው።

አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የኢትዮጵያንም ሆነ የአህጉሪቱን ችግሮች ለመፍታት ሁነኛ መፍትሄ እንዲሁም የወደፊት የዓለም የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አንስተዋል።

ይህንንም ተከትሎ እንደ ደስታ ሮቦት ያሉ የሰው ሰራሽ አስተውሎቶችን በመፍጠር ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ግንባታ የሚሰጠው ትኩረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።


 

ደስታ ሮቦት የዛሬውን የሙዚቃ መርኃ ግብር እንድታሰናዳ የተደረገው የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስና አይኮግ ላብስ ከኢትዮጵያ አየር መንገድና ኢትዮ-ቴሌኮም ጋር በመተባበር ነው።

ደስታ ሮቦት የአማርኛ ቋንቋን መናገር የሚያስችል ፕሮግራም የተጫነላት ሲሆን በመርኃ ግብሩ በአማርኛ ንግግር አሰምታለች።

የኢትዮ-ቴሌኮም 5ኛ ትውልድ ቴክኖሎጂን በመጠቀምና በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በቋንቋ ቅንብር አማርኛ ቋንቋ የምትናገረው ደስታ ሮቦት በአይኮግ ላብስ ነው የለማችው።

ደስታ የአማርኛ ቋንቋን የምትናገር፣ የግርምት፣ ደስታና ሌሎች ስሜቶችን የምታንጸባርቅ ብሎም መደነስ የምትችል ሮቦት ናት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም