ማዕከሉ የአፍሪካ የካይዘን ፍልስፍና ቴክኖሎጂ የብቃት ማዕከል ለመሆን እየሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ካይዘን ልህቀት ማዕከል የአፍሪካ የካይዘን ፍልስፍና ቴክኖሎጂ የብቃት ማዕከል ለመሆን እየሰራ መሆኑን ገለጸ።

የማዕከሉ ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ምንዳዬ ይርጋ ለኢዜአ እንዳሉት ማዕከሉ የካይዘን ፍልስፍና ቴክኖሎጂዎችን በጥናትና ምርምር አስደግፎ በማስተላለፍ የአምራች ኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪነት ለማሻሻል እየሰራ ነው።

በሀገር በቀል ምጣኔ ሃብት ለውጥ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች አንዱ የሆነው የማምረቻው ዘርፍ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን በተለየ ትኩረት እየተሰራበት መሆኑን ተናግረዋል።

ማዕከሉ ጥራትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲሁም የአምራችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን የስራ ባህል ለማሻሻል በየአመቱ 150 በሚደርሱ ድርጅቶች ፍልስፍናውን ለማስረጽ እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ማዕከሉ የአፍሪካ የካይዘን ፍልስፍና ቴክኖሎጂ ልህቀት ማዕከል ለመሆን እየሰራ እንደሚገኝም ስራ አስኪያጁ አስታውቀዋል።

ከጃፓን መንግስት ጋር በመተባበር በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የሚገኙ ተቋማትን በካይዘን ፍልስፍና ቴክኖሎጂ ለማብቃት የሚረዳ ስልጠና ለመስጠት እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ማዕከሉ የአፍሪካ ሀገራት የምጣኔ ሃብት ዘርፋቸውን ምርታማና ተወዳዳሪ እንዲያደርጉ ስልጠናዎችን መስጠት የሚያስችል የሰው ሃይልና ዝግጁነት አለው ብለዋል።

ማዕከሉ 11 አነስተኛ ማሰልጠኛ ክፍሎች እንዳሉትና በዚህም በአንድ ጊዜ እስከ 440 ሰልጣኞችን ማስተናገድ እንደሚችል ገልጸዋል።

በተጨማሪም ዘመናዊ ካፍቴሪያዎች፣ የመኝታ ክፍሎችና ሌሎች አስፈላጊ ግብአቶችን አሟልቶ የተገነባ በመሆኑ በሀገር አቀፍ እንዲሁም አህጉር አቀፍ ደረጃ ስልጠናዎችን የመስጠት ብቃት አለው ብለዋለ።

ማዕከሉ በጃፓን መንግስት ድጋፍ ተገንብቶ መስከረም 27 ቀን 2016 ዓ.ም መመረቁ ይታወሳል።

የካይዘን ፍልስፍና በጥራት፣ ቦታ አጠቃቀም፣ የሃብት ብክነት፣ ወጭና ሌሎች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ሃብትን በአግባቡ ተጠቅሞ ውጤታማና ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያግዝ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም