ደስታ የተሰኘች ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም ለእይታ ቀረበች

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 2/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እና አይኮግ ላብስ ከሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር ደስታ የተሰኘች ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም ለእይታ አቀረቡ።

ህፃናት፣ ወጣቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በሳይንስ ሙዚየም በመገኘት የደስታ ሮቦትን ጨምሮ በስታርት አፕ ኤግዚቢሽን የቀረቡ ስራዎችን እየጎበኙ ነው።

በዚህ ወቅት የገንዘብ ሚኒስቴር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እንዳሉት ኢትዮጵያ ዓለም የደረሰበት አዲሱ የቴክኖሎጂ እውቀት የሆነው ሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ በትኩረት እየሰራች ነው።


 

ደስታ ሮቦትም በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት አማርኛ እንድትናገር ተደርጋ መቅረቧን አንስተው፥ ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዓለም የደረሰበት ደረጃ ለመድረስ እየሰራች መሆኑን ጠቅሰዋል።

ደስታ ሮቦት በዛሬው እለት በሳይንስ ሙዚየም ከምታደርገው ቆይታ ባለፈ በነገው እለት ከአርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ ጋር የጃዝ ምሽት እንደሚኖራት ተገልጿል።

በመጪው አርብ ደግሞ በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ከሌሎች በኢንስቲትዩቱ ከተሰሩ ሮቦቶች ጋር ለዕይታ እንደምትቀርብ ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም