መንግስት ለስታርት አፖች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እያከናወናቸው ያሉ ማሻሻያዎች ዘርፉ ይበልጥ እንዲነቃቃ የሚያደርጉ ናቸው

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 1/2016(ኢዜአ)፦ መንግስት ለስታርት አፖች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እያከናወናቸው ያሉ ማሻሻያዎች ዘርፉ ይበልጥ እንዲነቃቃ የሚያደርግ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው ስታርት አፖች ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ "ስታርት አፕ" ኤግዚቢሽን የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ትናንት በሳይንስ ሙዚየም ተከፍቷል።


 

በኤግዚቢሽኑም በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በኢነርጂ፣ በኢንዱስትሪ፣ በፋይናንስና በሌሎች ዘርፍ የተሰማሩ በመጀመሪያ ደረጃ የሚገኙ፣ የመጀመሪያ ደረጃን የተሻገሩና ወደ ገበያ  የተቀላቀሉ ስታርት አፖች የፈጠራ ውጤታቸውን አቅርበዋል።

በኤግዚቢሽኑ "እርሻ" የተሰኘ ዲጂታል መተግበሪያ ይዛ የቀረበችው ሜሮን ስለሺ፤ መተግበሪያው አርሶ አደሮችን  ከእርሻ ግብዓትና የሜካናይዜሽን አገልግሎት አቅራቢዎች ጋር የሚያገናኝ ነው።

እንዲሁም አርሶ አደሮች ተለዋዋጭ የአግሮ-አየር ንብረት ምክር እንዲጠይቁ የሚያስችል ዲጂታል መድረክ ነው ብላለች ።

ለዚህ ደግሞ የሞባይል መተግበሪያን ፣ የጥሪ ማዕከል እና ወኪሎችን ያጣመረ መሆኑን ተናግራለች።

ስታርት አፖች አዲስ ሃሳብ ይዘው ወደ ማህበረሰቡ ለመግባት ጊዜ እንደሚወስድ ጠቅሳ ፤  መንግስት እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት  ስታርት አፖችን ለማስተዋወቅ እና የበለጠ እንዲሰሩ የሚያግዝ እንደሆነ ገልፃለች።


 

የኖሊጋ ኢንጂነሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ኦፕሬሽን ኃላፊ ካሳ ደጀኔ በኤግዚቢሽኑ ከማንኛውም ወራጅ ውሃ ሃይል ማመንጨት የሚያስችል ተርባይን እና ከንፋስ በቀላሉ ሃይል ማመጨት የሚያስችል ፈጠራ ስራ ይዘው መቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡

የፈጠራ ስራዎችን በሚያከናወኑበት ወቅት ከመንግስት የፋይናንስ ድጋፍ ማግኘታቸውን ጠቅሰው፤ በአጠቃላይ በመንግስት የተወሰዱት አዳዲስ የህግ ማሻሻያዎችን ለስታርት አፕ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ መሆናቸውን  ተናግረዋል።

የሲምቦና አፍሪካ መስራች ሃና ብርሃኑ በበኩሏ ሲምቦና አፍሪካ በኢትዮጵያ ውስጥ የህክምና መሳሪያዎችን ማምረት ላይ የሚሰራ ሜድቴክ ኩባንያ  መሆኑን ተናግራለች።


 

በኤግዚቢሽኑ ዩ.ቪ.ሲ. ስትራላይዘር መሳሪያ፣ የፎቶ ቴራፒ መሳሪያ፣ የጨቅላ ህፃናት ማሞቂያ ኦክስጅን  ይዘው መቅረባቸውን ተናግራለች።

እነዚህን ስራዎች በሚያከናውኑበት ወቅት የፋይናስ ችግር ሲያጋጥማቸው እንደነበር ጠቅሳ፤ መንግስት ይህን ለመቅረፍ እያከናወነ ያለው ተግባራት ስታርት አፖችን የሚያበረታታ ነው ብላለች።

ባሳለፍነው ሳምንት በዓድዋ መታሰቢያ በተካሄደው  “የኢትዮጵያ ስታርት አፕ ብሔራዊ ሁነት” ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "ፈጠራ ላይ የተመሰረተና የመፍትሔ ሃሳብ ያላቸውን ስታርት አፖች መደገፍ ኢንቨስትመንት እንጂ እርዳታ አይደለም" በማለት መልዕክት ማስተላለፋቸው ይታወቃል፡፡ 

በመድረኩም መንግስት ለስታርት አፖች ምቹ ምህዳር መፍጠር የሚያስችሉ ዘጠኝ የአሰራር ማሻሻያዎችን ይፋ አድርጓል፡፡

ማሻሻያዎቹ ከዚህ ቀደም የነበሩ የአሰራር ማነቆዎችን እንደሚፈቱም ነው የተገለጸው፡፡

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም