የ'ስማርት አዳማ' ፕሮጀክት በከተማው አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ለማምጣት አስችሏል-- አቶ ሀይሉ ጀልዴ

አዳማ፣መጋቢት 26/2016(ኢዜአ)የ'ስማርት አዳማ' ፕሮጀክት በከተማው አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ማስቻሉን የከተማው ከንቲባ አቶ ሀይሉ ጀልዴ አስታወቁ።

የ'ስማርት አዳማ' ፕሮጀክት የሶስት ዓመት አፈፃፀምና ቀጣይ የዲጂታል አገልግሎት ትግበራን የተመለከተ ውይይት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተካሄዷል።


 

የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የ'ስማርት አዳማ' ፕሮጀክት የተሻለ ውጤት እየተገኘበት ነው።

በተገኘው ውጤትም የኢትዮጵያ ከተሞች የዲጂታል አገልግሎትን ለማስፋፋት ከአዳማ ከተማ ልምድ እየቀሰሙ መሆኑን ተናግረዋል።

በ'ስማርት አዳማ' የእስካሁን አፈፃፀም በአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ላይ ለውጥ መምጣቱን ገልጸው በዚህም ብልሹ አሰራርና ሌብነትን ከማስወገድና የህዝቡን ቅሬታ ለመፍታት ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ጠቁመዋል።

የ'ስማርት አዳማ' ግብ ዘመናዊና ዲጂታል አገልግሎትን በሁሉም ዘርፎች መተግበር መሆኑን ያስታወሱት ከንቲባው በዚህ ረገድም ዘርፈ ብዙ ስራዎች ተሰርተዋል ነው ያሉት።

በተለይም መሬት፣ ገቢዎች፣ ትራንስፖርት፣ ውሃና ፍሳሽ፣ ንግድ፣ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት፣ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት፣ የትራፊክ አገልግሎት፣ የፍትህ እንዲሁም የከተማዋን ሰላም በቴክኖሎጂ ታግዞ ለመጠበቅ ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።

በወቅቱ ሀሳቡ ተግባራዊ መደረግ ሲጀመር ብዙ ችግሮች እንደነበሩ አንስተው አሁን ግን ተጨባጭ ውጤት እየታየበት መሆኑን ተናግረዋል።

በኦሮሚያ መሬት ቢሮ የፕላንና ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ይልማ ሲሳይ የ'ስማርት አዳማ' ፕሮጀክት ከተማው በተለይም በመሬት አስተዳደር ዘርፍ ለህብረተሰቡ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ወደ ዘመናዊ አሰራር መቀየር እንዳስቻለ ተናግረዋል።

ባለፉት ሶስት ዓመታት ከመሬት አስተዳደር ጀምሮ በተለያዩ ዘርፎች የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን የተሰራው ስራ ውጤት ከማስገኘቱም ባለፈ ለሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ሞዴል እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል።

በዚህም መስተዳድሩ ከ519 ሺህ በላይ የመሬት ይዞታ ፋይሎችን ወደ ዲጂታል በማስገባት የቀጥታ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።

በአዳማ በዲጂታላይዜሽን አገልግሎት የታየውን ውጤትና ተሞክሮ ከ30 በላይ በሚሆኑ የክልሉ ከተሞችና 124 ወረዳዎች የማስፋፋት ስራ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

በ23 ዋና ዋና የክልሉ ከተሞች የመሬት ይዞታ የካዳስተር ምዝገባ ስራ ዘንድሮ እንደሚጠናቀቅ የገለጹት አቶ ይልማ በቀጣይ ከወረቀት ንክኪ ነፃ የሆነ ዲጂታል አገልግሎት በሁሉም ከተሞች ተደራሽ የሚደረግ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።

በየደረጃው ባለው የመሬት መዋቅር ውስጥ ያለውን የህዝብ ቅሬታ ከመሰረቱ ለማስወገድ አዳማ ከተማ ላይ የተጀመረውን የዲጂታላይዜሽን የአሰራር ስርዓት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም