ብሔራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት የመጀመሪያ ስብሰባውን አካሄደ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 4/2016(ኢዜአ):- ብሔራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት የመጀመሪያ ስብሰባውን አካሂዷል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር በለጠ ሞላ በዚሁ ወቅት፤ ምክር ቤቱ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ እና ስራዎቹን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በየጊዜው ሪፖርት እንደሚያደርግ አብራርተዋል፡፡

የምክር ቤቱ በ1205/2012 የፀደቀው የኤሌክትሮኒክስ ግብይት አዋጅ መሰረት አድርጎ የተቋቋመ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሚመለከታቸው ተቋማት እና ባለድርሻ አካላት የምክር ቤቱ አባላት እንደሆኑም ተናግረዋል።


 

ምክር ቤቱ ቅንጅታዊ አስራርን በመዘርጋት አስፈላጊ የሆኑ ስራዎችን በመለየት የፖሊሲ እና የስትራቴጂ ምክረ ሃሳብ በማቅረብ እና የወጡ ፖሊሲዎች ውጤታማነት የሚገመግም መሆኑንም እንዲሁ፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ የወጡ የዲጂታል እና ቴክኖሎጂ ፓሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች ተፈፃሚነታቸውን በየጊዜው መከታተል አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ምክር ቤቱ ይህንን ታሳቢ በማድረግ መደራጀቱን ጠቁመዋል፡፡

ይህም የኢትዮጵያን ዲጂታል ጉዞ ውጤታማ በማድረግ ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የወጡ ፖሊሲዎች በውጤታማነት እንዲተገበሩ የመከታተል ተግባራትንም እንደሚያከናውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡


 

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ በበኩላቸው ምክር ቤቱ ቅንጅታዊ አስራርን በማጎልበት በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዘርፍ ኢትዮጵያ ያቀደቻቸውን ዕቅዶች እንድታሳካ የሚያስችል ነው ብለዋል።


 

ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 እውን ለማድረግ የተጀመሩ ተግባራትን የበለጠ የሚያጠናክርበት ዙሪያ ላይ እንደሚሰራ የተናገሩት ደግሞ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ናቸው፡፡

ምክር ቤቱ በዛሬ ስብሰባው ቀደም ብሎ ተቋቁሞ በነበረው ግብረ ሃይል የተሰሩ ስራዎችን ሂደት የተመለከተ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይ በሚሰሩ ስራዎች ዙሪያ አቅጣጫ ማስቀመጡንም ጠቁመዋል፡፡

እስካሁን ባለው ሂደትም ከ132 ተቋማት መካከል 108 የሚሆኑት ወደ ዲጂታል ዳታ ማዕከል መረጃቸውን ማስገባታቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም